ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ውስጣዊ አንድነት ማጎልበት ወሳኝ ነው... ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ውስጣዊ አንድነት ማጎልበት ወሳኝ ነው... ምሁራን
መቐለ ፣ ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድነትና የጥንካሬ መገለጫ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገር ጥቅም እንዲውል ከግንባታው ጎን ለጎን ውስጣዊ ጥንካሬ ማሳደግ እንደሚገባ ሙሁራን ገልፁ።
በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲክ ሳይንስ አለም አቀፍ ግንኝነት ምሁር የማነ ዘርአይ ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ፣በሱዳንና ግብጽ መካከል የሚደረጉ ድርድሮች በጥንቃቄ መመራት አለበት።
ለዘመናት ግብፅና ሱዳን ለብቻቸው ሲጠቀሙበት የነበረው የአባይ ውኃ ኢትዮጵያ የአቅም ለውጥ ስታመጣ የአጠቃቀም ለውጥም አብሮ መምጣቱ ምሁሩ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የታየውን እድገት ተከትሎ በወንዙ የመጠቀም ፍላጎቷ መጨመሩ ለራሷብቻ ሳይሆን በላይኛው የተፋሰስ አገሮች ጭምር መነሳሳት መፍጠሩን ምሁሩ ተናግረዋል።
ይህ የሚያመላክተው ውስጣዊ አቅምና ጥንካሬ እያደገ በመጣ ቁጥር ፍላጎትህን ለማሳካትም ሆነ ተፅእኖ የመፍጠር አቅምህ እንደሚጨምር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ የህዝቡን የጥንካሬና የአንድነት መገለጫ መሆኑን የተናገሩት ምሁሩ የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ለውጤት እንዲባቃ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት መልእክት አስተላልፈዋል።
የውስጥ አቅም መጎልበት በሌሎች ዘንድም የተለየ ገፅታ ያላብሳል ያሉት ምሁሩ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ግድቡን መገንባት መጀመሯ በሌሎች ታዛቢ አካላት ዘንድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን ገልፀዋል።
አገሪቷ የምትፈልገውን ልማት ለማጠናከር በኢኮኖሚ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ወታደራዊና የነዚህ ውጤት በሆነው ድፕሎማሲያዊ ጉዞ ጠንካራ የኃይል ሚዛን መፍጠር እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።
የናይል ተፋሰስ በቀጠናው ለሚገኙ አገራት ፋይዳው ቀላል ባለመሆኑ ድርድሩን በዋነኛነት የአፍሪካ ህብረትና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት/ኢጋድ / በቅርበት ሊመሩት ይገባል ብለዋል።
በኢኮኖሚ ያደጉ አገራት ሜጋ ፕሮጀክቶቻቸው በሚያገኙት ብድር እንደሚገነቡ የተናገሩት ደግሞ በህዳሴ ግድብ በርካታ ጥናት ያደረጉና የጂኦግራፊ ምሁር ብርሀኑ በላቸው ናቸው።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በራስ አቅም ተገንብቶ ለፍጻሜ መቃረቡ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልዩ ስፍራ አለው ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ፍፃሜ መቃረብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጥረቱን ውጤት የሚያይበት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ የሚያደርሳት ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ለአገራችን ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ በአፍሪካ የነበረን የፖለቲካ ተሰሚነት የሚያስቀጥል መሆኑንም አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል።
ግድቡ የአፍሪካ አገራት ህዝቦችን በማስተባበር ሁሉንም ነገር መስራት እንደሚቻል የሚያሳይ ይሆናል ብለዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ያሳየውን መንፈስ እስከ ግድቡ ግንባታ ፍፃሜው ድረስ በመዝለቅ በአለም መድረክ ላይ ደማቅ ታሪክ መፃፍ ይኖርበታል ብለዋል።