ቀጥታ፡

በአዲሱ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ ምሁራን ምልከታ

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 በአዲሱ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ ምሁራን ምን ይላሉ? ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990 ዓ.ም ደም አፋሳሽ ጦርነት ካደረጉ በኋላ ላለፉት 20 ዓመታት ሰላምም ሆነ ጦርነት አልባ ግንኙነቶችን ማሳለፋቸው ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከወራት በፊት ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተቀየረ መጥቷል። በአገራቱ አዲስ ግንኙነት ቀጣይነትና መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች የዘርፉ ምሁራን ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ምሁራኑ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የምታካሂደው አዲሱ ግንኙነት የህዝቡን ፍላጎትና ይሁንታ የሚያረጋግጥ አንዲሁም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚያስችል መንገድ ሁሉንም የሚያሳትፍ ማድረግ እንዳለበት ነው የገለጹት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ  እንደተናገሩት በሀገራቱ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር የሚያስችለው ሁኔታ ያለውጭ ጣልቃ ገብነት በራሳቸው በሁለቱ መንግሥታት ፍላጎት መጀመሩ መልካም ተግባር ነው። ያም ሆኖ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በቅድሚያ ሁለቱ መንግሥታት የመተማመኛ ውሎች ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ነው ፕሮፌሰሩ የሚናገሩት። በኢትዮጵያና ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተጀመረው ጥረት በሀገራቱ ህዝቦች መካከል ያለው ተፈጥራዊ ወንድማማችነት ወደነበረበት ከመመለስ በሻገር የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅሞችን የሚያስጠብቅ መሆን አለበት ሲሉም ፕሮፌሰር ካሳሁን ገልፀዋል። በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳዮች ላይ የተለያዩይ ምርምር ያደረጉት ጀነራል አበበ ተክለኃይማኖት በበኩላቸው ከዚህ በፊት ለሁለቱም አገራት ህዝቦች አስቸጋሪ በነበሩ ጉዳዮች ላይ ህዝቡ ራሱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንዲጠቁም የሚያስችል አሰራሮችን መከተል አስፈላጊ ነው ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ያእቆብ አርሳኖ እንዳሉት የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ጉዳይ የመንግስታቱ ብቻ ሳይሆን የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ጉዳይም ጭምር በመሆኑ ይሁንታቸውን መሻት የግድ ይላል። መንግስት የወሰን ማካለልን ጨምሮ የምጣኔ ኃብትና ፖለቲካዊ ስምምነቶችን ሲፈጽም በየደረጃው ያለው የህብረተሰብ ክፍልን፣ ምሁራንን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ የህዝብ እንደራሴዎችንና የመንግስት ኃላፊዎችን የማሳተፍና የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት ይላሉ ዶክተር ያእቆብ ። ምሁራኑ ሂደቱን አስመልክቶ በቀጣይ መደረግ ስላሉባቸው ቀሪ ስራዎች ምክረ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በሰላም ድርድር ሂደቱ ዘላቂ ሰላም ከማምጣት ባሻገር የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ጥቅምንና መብትን ለማረጋገጥ እንዲቻለው የማህበረሰቡንና የልሂቃን ተወካዮችን ያካተተ ኮሚቴ እንዲያቋቋም ጀነራል አበበ አሳስበዋል። ዶክተር ያእቆብ በበኩላቸው የሰላም ድርድር ሂደቱ የሚያነሳቸው ነጥቦች  ከቀላል ወደ ከባድ ዝርዝር ጉዳዮች የሚሸጋገር ሂደትን መከተል  እንዳለበት ተናግረዋል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የቆየው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግስት ባቀረበው ጥሪ መሰረት ተቋርጦ የነበረው የሀገራቱ ግንኙነት እየተሻሻለ መጥቷል። በዚህም መሰረት የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት የልዑካን ቡድንም በቅርቡ ወደ አስመራ ይጓዛል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም