ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ በቀን ለ14 ሺህ ሰው የኮቪድ-19 ምርመራ ለማድረግ አቅዳለች

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2021(ኢዜአ) ኢትዮጵያ አሁን ያላትን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የመመርመር አቅሟን ከሐምሌ ወር ጀምሮ በቀን ወደ 14 ሺህ ሰው ለማድረስ እየሰራች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ያካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከአባላቱ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጤና፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በመንግስት ምን አይነት እርምጃ እየተወሰደ ነው? የሚልና ሌሎች ጥያቄዎች ይገኙበታል።

ከሶስት ወራት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ ናሙና በመላክ የምርመራ ውጤት የመቀበል ደረጃ ላይ እንደነበር አስታውሰው፤ የላቦራቶሪ የመመርመር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካሉት 31 የምርምራ ማዕከላት በተጨማሪ በተያዘው ወር 15 ተጨማሪ ማዕከላት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመው፤ በሐምሌ ወር የመመርመር አቅሙ በቀን 14 ሺህ ሰው እንደሚደስ ገልጸዋል።

17 ሺህ 500 የኮቪድ-19 ታማሚዎችን ማስተናገድ የሚችሉ 54 የሕክምና ማዕከላት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

የቫይረሱ ምልክት የታየባቸው 30 ሺህ ገደማ ሰዎች በለይቶ ማቆየት የሚችሉና፣ አቅም ለሌላቸው 45 ሺህ ኢትዮጵያዊያንም የለይቶ ማቆያ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ሞሮኮ ቀጥላ ብዙ ሰው የመረመረች ቢሆንም፣ ከሕዝብ ብዛቷ አንጻር አነስተኛ በመሆኑ የምርመራ አቅምን የማሳደግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚከወኑ ስራዎችን አስመልክቶ መንግስት የሚያውቀውን ነገር ያለምንም ድብብቆሽ ለሕዝብ ተደራሽ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በህብረተሰቡ ዘንድ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያደርገው ጥንቃቄ መዘናጋት እንደሚስተዋልበት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህብረተሰቡ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመሳሳይ ኢኮኖሚውን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ባለፉት 10 ወራት ወደ ውጭ በተላኩት ቡና፣ አበባና ሌሎች ምርቶች የ13 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል።

''ኮቪድ-19 በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ካሳደረው ተጽዕኖ ባሻገር የወጪ ንግዱ እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል'' ብለዋል።


ባለፉት 10 ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 667 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንና ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን በመግለጽ።

ከስጋ ምርት የተገኘው 45 ሚሊዮን ዶላር ገቢም የ21 በመቶ ጭማሪ አለው ብለዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ባለው ከፍተኛ የስጋ ፍላጎት በአገር መሪዎች ደረጃ ጭምር ተጨማሪ ጥራት ያለው ስጋ እንዲቀርብ መጠየቁን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ወደ ውጭ ከተላከ የወርቅ ምርት 27 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፤ ይህም የ19 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።

ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ምርቶች በተለይ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ለዚሁ ግዥ ይውል የነበረው ወጪ ሌሎች ምርቶችን ለመግዛት እንዳስቻለም አክለዋል።

በአንጻሩ የኮሮናቫይረስ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩንና የአገልግሎት ዘርፉም መጎዳቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

የግብርና ዘርፍ ስራዎችን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

በኩታ ገጠም የተጀመረውን የእርሻ ስራ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፤ ለአብነትም በአርሲ አካባቢ በኩታ ገጠም የተሰራው የእርሻ ስራ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጤፍ በማምረት የሚታወቁ የሸዋ አካባቢዎች አሁን በስፋት አቦካዶ ማምረት መጀመራቸውን ገልጸው፤ አቦካዶ ከአመታት በኋላ የቡናን ያህል በወጪ ንግድ ገቢ የማስገኘት አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

በቆላማ ቦታዎች እርሻዎች ዘንድሮ 20 ሺህ ያህል ሄክታር በማልማት በሄክታር በአማካኝ 42 ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል። በዚህም ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ሊገኝ መቻሉን ተናግረዋል።

14 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በዚህ አመት ለማስገባት ዕቅድ መያዙን ገልጸው፤ ''ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና ከወደብ ሎጂስቲክ ውስንነት ጋር ተያይዞ በተወሰነ ደረጃ ችግር የገጠመ ቢሆንም እስካሁን 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ክልሎች ጋር ደርሷል'' ብለዋል።

''1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት ውስጥ የሚገባ ይሆናል'' ነው ያሉት። 

እንደወትሮው ሁሉ የምርጥ ዘር እጥረት ማጋጠሙ እንደማይቀር ጠቁመው፤ ሰፋፊ እርሻዎች ላይ የምርጥ ዘር ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለው መንግስት 'ጠንካራ አይደለም' የሚሉ አካላት አሉ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ የሚልም ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

እሳቸውም ሲመልሱ ምናልባት አሁን ያለው መንግስት ዜጎችን ስለማያንገላታና ሃሳቦችን ስለማያፍን ሊሆን ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።

በቀደሙት ጊዜያት ያለው መንግስት የጥበብ ስራን ሳንሱር እንደሚያደርግና ከአገር ውጪ ያሉትንም ሚዲያዎች መቆጣጠር ይፈልግ እንደነበረም ተናግረዋል።

ጣናን ከእምቦጭ ለመታደግ የክልሉ መንግስት በማሽንና በሰው ሃይል እንቦጭን ለመቀነሰ ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

''በቀጣይም በሰውና በማሽን የሚደረገውን ጥረት ባለማቋረጥ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ይሰራል'' ነው ያሉት።

''እስካሁን የተሞከሩ ማሽኖች ውጤታማ ስላልሆኑ የፌዴራል መንግስት ከአውሮፓ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የተሻለ ማሽን ለማምጣት እየተደራደረ ነው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም