የለውጡ አመራር ከፍተኛ ችግር ተጋርጦበት የነበረውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መለወጥ ችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡ አመራር ከፍተኛ ችግር ተጋርጦበት የነበረውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መለወጥ ችሏል
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1/2012 ( ኢዜአ) ከለውጡ በፊት በተለያዩ ችግሮች ተተብትቦ የነበረውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የለውጡ አመራር በብዙ መልኩ ለውጦት ግንባታው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።
ግድቡ በተያዘው ወር መጨረሻ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ መያዝ እንደሚጀምርም ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከመጀመሪያው ጀምሮ ችግር የነበረበት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጡ አመራር ከመጣ ወዲህ ግንባታው በፍጥነት እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያወጣ ፕሮጀክት እንደሆነና፤ ኢትዮጵያም አብሮ የመልማት እንጂ የሌሎች አገራትን ጥቅም የመንካት ፍላጎት የሌላት መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱን ለማፋጠን ከለውጡ ወዲህ የአመራሮችና የኮንትራት ለውጥ መደረጉን አንስተዋል።
በአንድ ዓመት ተኩል ብቻ የግድቡ ዋና አካል 35 ሜትር ከፍታ ያለው ግንባታ መካሄዱን ገልጸው፤ የለውጡ አመራር እስኪመጣ 25 ሜትር ከፍታ ብቻ በዋናው የግድቡ አካል ላይ መሰራቱን ጠቁመዋል።
የግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ከዜሮ የመጀመር ያህል ስራ መከናወኑንም ነው የተናገሩት።
ግድቡ በተያዘው የሰኔ ወር መጨረሻ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር ገልጸዋል።
የግድቡን ግንባታ በተመለከተ መሰረተ ቢስ ወሬ እንደሚናፈስና ግንባታው ከሚናፈሰው ወሬ በተቃራኒ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም አክለዋል።
በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር የተፈጠረው ክስተት ከምክር ቤቱ አባላት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ነው።
ለጉዳዩ መፍትሄ ለማበጀት መንግስት እየሰራ ያለው የዲፕሎማሲ ስራ ምን ይመስላል? የሚል ጥያቄ ተነስቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሰጡት ምላሽም ስለተፈጠረው ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋር ሰፊ ውይይት እያደረገ ነው ብለዋል።
መሰል ውይይቶች በቀጣይም እንደሚካሄዱና የሚነሱ ጉዳዮችን በሠላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በሱዳን በኩል ሚሊሻ ወደ አገራችን እየገባ ነው፣ ወደ መሬታችን እየገባችሁ ነው፣ ጉዳዩ በገላጋይ ዳኛ ይታይ የሚሉ ሃሳቦች እየተነሱ መሆናቸውንና ጥያቄዎቹም ተገቢ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይሁንና ጉዳዮቹ ጥይት ለመተኮስ የሚያደርሱ እንዳልሆኑና ችግሩን በድርድር ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።