በጋምቤላ በአዋጁ አፈፃፀም የሚታዩ ክፍተቶች ለማረም በቅንጅት ሊሰራ ይገባል -የክልሉ ርእሰ መስተዳድር - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ በአዋጁ አፈፃፀም የሚታዩ ክፍተቶች ለማረም በቅንጅት ሊሰራ ይገባል -የክልሉ ርእሰ መስተዳድር
ጋምቤላ፣ ሰኔ 1/ 2012 ዓም (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የተላለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበር ላይ የሚታዩ የአፈፃፀም ችግሮችን ለማረም ሁሉም በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አሳሰቡ ።
በክልሉ የኮሮና ወርርሽኝ ለመከላከል እየተካሄዱ የሚገኙ ስራዎች ላይ ግብረ ኃይሉ ግምገማ አካሄዷል።
የክልሉ ርዕሰ መሰተዳድርና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ ኡሞድ አጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የኮሮና ወርርሽኝን ለመከላከል የተላለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሉ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በርካታ ክፍተቶች ይታያሉ ።
በተለይም አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ፣ የአፍና የአፈንጫ መሸፈኛ ጭንብልን ከመጠቀምና ከአራት በላይ ሰው በአንድ ቦታ እንዳይሰበሰብ የተላለው ውሳኔ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ብለዋል።
በትራንስፖርት አገልገሎቱ ዘርፍም ተመሳሳይ የአፈፃፀም ችግርን ጨምሮ ሰፊ የመዘናጋት ምልክቶች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል።
በአዋጁ አፈፃፀም የሚታዩ ክፍተቶችና በህዝቡ አካባቢ የሚታዩ የመዘናጋት ችግሮች ያልተፈለገ ዋጋ ሊያስከፍሉ እንደሚችሉም ስጋታቸውን ገልፀዋል ።
በመሆኑም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚታዩ የአፈፃፀም ክፍተቶችን ለማረም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በትብብር ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል ።
በተለይም የጸጥታው ግብረ ኃይል በክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች ያለውን የሰዎች ዝውውርና የስደተኞች ፍልሰት ለመግታት ጭምር በትኩረት ሊሰራ ይገባል ።
የክልሉ ጤና ቢሮና የግብረ ኃይሉ አባል አቶ ካን ጋልዋክ በበኩላቸው ከአሁን በፊት በክልሉ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ በአዋጁ አተገባበርም ሆነ በህዝቡ ዘንድ መዘናጋት ተፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል ።
መዘናጋቱ ተገቢነት ስለሌለው በአዋጁ የተቀመጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የጸጥታ ኃይሉ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል ።