ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ዋና የህዝብ እምባ ጠባቂ ሆነው ተሾሙ - ኢዜአ አማርኛ
ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ዋና የህዝብ እምባ ጠባቂ ሆነው ተሾሙ
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶክተር እንዳለ ኃይሌን ዋና የህዝብ እምባ ጠባቂ አድርጎ ሾመ። ምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ ልዩ ስብሰባውን ዛሬ ያካሄደ ሲሆን የተለያዩ ሹመቶችንም ሰጥቷል። የቀድሞው የተቋሙ ዋና እምባ ጠባቂ ወይዘሮ ፎዝያ አሚን ወደ ሌላ መስሪያ ቤት መዛወራቸውን ተከትሎ ነው ዶክተር እንዳለ ወደ ሥልጣን የመጡት። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ስብሰባ 8 አባላት ያሉት እጩ አቅራቢ ኮሚቴ አቋቁሞ ነው ምርጫውን ያካሄደው። በዚሁ መሰረት ለሕገ-መንግሥቱ ተገዥ የሆነ፣በስነ ምግባሩ መልካም ስም ያተረፈና የወንጀል ጥፋት የሌለበት የሚሉ መስፈርቶች ከግምት ውስጥ መግባታቸው ታውቋል። ዕጩ ሆነው ከቀረቡት 77 ሰዎች መካከል ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ተመርጠው በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ከጸደቀ በኋላ ቃላ መሀላ ፈጽመዋል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ ለሰመራና ጋምቤላ እምባ ጠባቂ ቅርንጫፎች ኃላፊዎችን ሾሟል። ወይዘሮ መሰረት ማሞ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሴቶችና ህጻናት ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።