የኮሮና ቫይረስ ወደ ስደተኞች መጠለያዎች እንዳይገባ የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮና ቫይረስ ወደ ስደተኞች መጠለያዎች እንዳይገባ የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ1/2012(ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በድንበር አካባቢ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች እንዳይገባ ጠንካራ የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የኢትዮጵያ የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ገለጸ።
ኢትዮጵያ መጠለያ በመስጠት እያኖረቻቸው የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር ወደ 945 ሺህ ይጠጋል።
የኮሮናቫይረስ የሰዎችን ጥግግት የማይፈቅድና በተቃራኒው መራራቅን ተግባራዊ ማድረግን የሚያስገድድ ነው።
የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ደግሞ በርካታ ሰዎች በአንድ መጠለያ ተፋፍገው እንዲኖሩ ግድ ይላሉ።
ይህ የአኗኗር ሁኔታ ታዲያ ስደተኞች ዓለም አቀፍ ስጋት ሆኖ እየተስፋፋ ላለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ስጋት አሳድሯል።
በመሆኑም ችግሩ ተከስቶ አስከፊ ውጤት ከመከተሉ በፊት የቅድመ መከላከልና የዝግጅት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተሰሩ ስለመሆኑ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ ለኢዜአ እንደገለጹት ስደተኞቹ የችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ስራዎች ተጀምረዋል።
መጪው ክረምት መሆኑን ተከትሎ ስጋቱን በእጥፍ ስለሚጨምረው መጠለያዎችን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ድንበር አቋርጠው የሚመጡ ስደተኞች እንዳይገቡ የሚታገድ ሲሆን አምልጠው ቢገቡ እንኳ ለይቶ ማቆያ ስፍራ በሁሉም መጠለያዎች አሉ ብለዋል።
የመጠለያ ካምፖችን የማስፋት ስራ እየተሰራ ቢሆንም ካለው የሃብት ውስንነት አኳያ አቅም ያላቸው ወጣቶች ወደ ከተማ ሄደው እንዲሰሩ ፍቃድ እንደሚሰጥ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ስደተኞች ከአንድ መጠለያ ወደ ሌላ እንዳይዘዋወሩ መደረጉንም አክለዋል።
ውሃ በሌለባቸው ስፍራዎች ውሃ እንዲወጣ አልያም በቦቴ እንዲቀርብ፤ በመጠለያው ያሉ ዜጎች ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ እየተደረገ መሆኑንና በዚህም የተሳካ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።
በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋር፣ ሱማሌና ትግራይ ክልሎች ለሚገኙት ስደተኞች የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ አስፈላጊ ግብዓቶች መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት እየተሰባሰበ ይገኛልም ተብሏል።