አየር መንገዱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማእከል መሆኗን አረጋግጧል - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማእከል መሆኗን አረጋግጧል
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማእከል መሆኗን እንዳረጋገጠ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡
የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል የሚወሰዱ የእንቅስቃሴ ገደብ ውሳኔዎች ጥንቃቄ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ እያካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።
ከምክር ቤቱ አባላት ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከልም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የነበረውን ጫና ለመቀነስ የወሰዳቸው እርምጃዎች ምን ምን ነበሩ? የሚለው ይገኝበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ''መንግስትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በወሰዷቸው እርምጃዎች አየር መንገዱ በርካታ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል'' ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ አለማቆሙን አስታውሰው፤ አየር መንገዱ በችግር ጊዜ በረራ ባለማቆሙ ቻይና አሁን ላይ ከአየር መንገዱ ጋር ለመስራት መወሰኗንም ጠቁመዋል፡፡
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ግብታዊ የሆነ ውሳኔ ያሳለፉ በርካታ የአለም በተለይም የአፍሪካ አገሮች በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳታቸውን ተናግረው፤ አገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ሳያመሳክሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማቋረጥ መወሰን ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ የማያቋርጥ ከኮቪድ-19 በኋላም የያዘውን መልካም ስምና ዝና የሚያስቀጥልበት ተግባር መፈጸሙን ጠቅሰው፤ ''ወደብ አልባ የሆነችውን ኢትዮጵያ የአፍሪካ መገናኛ መሆኗን አረጋግጧል'' ብለዋል።
''ምርጥ አየር መንገድ፣ አስተዳደር እና ሰራተኞች ስላሉን የአፍሪካ ማዕከል መሆን ወደ ተቻለበት ደረጃ ደርሰናል'' ብለዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የእንቅስቃሴ ገደብ እርምጃ በተመለከተም ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ጋር ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።
በምክክሩም እንቅስቃሴን ሙሉ ለሙሉ የመዝጋት እርምጃ የሚወሰድባቸው ጉዳዮች በርጋታ መታየት እንዳለባቸው ተመክሯል።
ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴን በፍጥነት የመዝጋት ውሳኔ ያሳለፉ የአለም በተለይም የአፍሪካ አገሮች ዜጎቻቸውን ለአራት ቀናት ብቻ መመገብ እንደቻሉ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአምስተኛው ቀን ለችግር የተጋለጡበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንቅስቃሴን ከመዝጋት ይልቅ ወረርሽኙን ለመከላከል ተገቢ የሆኑ መረጃዎችን ማድረስ፣ የህክምና ስርዓትን ማዘመን፣ በኢኮኖሚው ላይም አደጋ እንዳይከሰት ሁሉም ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል እየወሰደች ያለችው መንገድ በከፍተኛ ሁኔታ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ግብታዊ እርምጃ መውሰድ የከፋ ችግር እንደሚያስከትል ገልጸው፤ እስካሁን እየተሄደበት ያለው መንገድ ግን በእጅጉ የሚያስመሰግን መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሆኖ ወረርሽኙን በጋራ ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግና ከመንግስትም የሚሰጡ ምክሮችንና መረጃዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የመከላከል ጥረቱ ውጤት እንዲያመጣ ዜጎች ሁለንተናዊ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡