ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ችግረኛ ለሆኑ 400 ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ

ሐረር ፣ ሰኔ 1/2012 ( ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ተጽዕኖ ለችግር ለተጋለጡ 400 አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረጉት የአቶ በላይ ሀብተ ጊዮርጊስ ባለቤትና ልጆች ቤተሰብ ናቸው።

ቤተሰቡን ወክለው ድጋፉን  ለክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ያስረከቡት አቶ ታምራት በላይ እንደተናገሩት ወቅቱ ወረርሽኙን ከመከላከል  ባሻገር መደጋገፍንና መተጋገዝን የሚጠይቅ ነው።

"በዚህም በክልሉ ቫይረሱ  ባስከተለው ተጽዕኖ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን መደገፍ ተገቢና በተለይ ከባለሀብቱ የሚጠበቅ ተግባር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

የአቶ በላይ ቤተሰብ ችግሩን በመረዳት ለ400 አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ከግማሽ ሚሊየን  ብር በላይ ወጪ በማድረግ የገዛው የማካሮኒ ፣ዱቄት እና  የምግብ ዘይት ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

በቀጣይም  የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ወረርሽኙን ከመከላከሉ በተጓዳኝ ቫይረሱ ባስከተለው ተጽዕኖ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት የበላይ ቤተሰብ በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ተጽዕኖ ለተቸገሩ ሰዎች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሌሎች ባለሀብቶችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ  ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የሐኪም ጋራ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ባዩሽ ተሰማ በሰጡት አስተያየት በተሰጣቸው እርዳታ መደሰታቸውን በመግለጽ ባለሀብቱን አመስግነዋል።

"በታቸለ አቅምም እራሳችንን በቤት እየቆየን  በመንግስትና ጤና ባለሙያዎች  የሚተላለፉ መመሪያዎችን በመተግበር ቫይረሱን ለመከላከል ጥረት እያደረግን ነው " ብለዋል።

የሸንኮር ወረዳ ነዋሪ  ወይዘሮ አዲስአለም ሰለሞን በበኩላቸው ድጋፉም በአሁኑ ወቅት ያጋጠማቸውን ወቅታዊ ችግር ለማለፍ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

በድጋፍ አሰጣጡ ስነስርዓት ወቅት በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ድጋፍ ላደረጉ ስምንት ግለሰቦችና ድርጅቶች ግብረ ኃይሉ ያዘጋጀላቸው  የእውቅና ምስክር ወረቀት ከርዕሰ መስተዳድሩ እጅ ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም