የህዳሴው ግድብ በሱዳንና በግብጽ ካሉ ግድቦች በደህንነት ደረጃ የተሻለ ነው ... የሱዳን የውሃ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴው ግድብ በሱዳንና በግብጽ ካሉ ግድቦች በደህንነት ደረጃ የተሻለ ነው ... የሱዳን የውሃ ሚኒስትር
ሰኔ 1/2012(ኢዜአ) ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሱዳንና ግብጽ ውስጥ ካሉት ግድቦች በደህንነት ደረጃ የተሻለ መሆኑን የሱዳን የመስኖና ውሃ ሃብቶች ሚኒስትር ያሲር አባስ ገለፁ፡፡
ሚኒስትሩ የህዳሴው ግድብ ከሱዳን በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ስለሚኖረው አስፈላጊነትም ከሃገራቸው ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል፡፡
የሱዳን የመስኖና ውሃ ሃብቶች ሚኒስትር በቆይታቸው “የህዳሴው ግድብ የደህንነት ደረጃ ከሱዳን ግድቦች እና ከፍታ ካላቸው የግብጽ ግድቦች በደህንነት ደረጃ የተሻለ ስለመሆኑ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ” ነው ያብራሩት፡፡
ሚኒስትሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሁለቱ ሀገራት ግድቦች የተሻለ የሚያደርገው በግንባታው ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ቁሳቁሶች እና ቴክኖሎጂዎችን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡
“ለራሳችን ጥቅሞች ብቻ ነው የምንወግነው፤ ውግንናችን አንዳንድ ጊዜ ከግብጽ ወይ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ሊሄድ ይችላል፤ግድቡ እንደሚጠቅመን ስንናገር ከኢትዮጵያ ጎን እንደቆምን ተደርገን እንከሰሳለን” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ላይ “የጎላ ጉዳት” እንደማያስከትል በተደጋጋሚ ስትገልጽ ግብፅ፤በበኩሏ የህዳሴ ግድቡ የውሃ መጠኗን ይቀንሰዋል የሚል አቋም ስታንፀባርቅ መቆየቷ ይታወሳል፡፡
ሶስቱ ሀገራት በግድቡ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡