የህዳሴ ግድብ በሰኔ ወር መጨረሻ ውሃ መያዝ ይጀምራል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ በሰኔ ወር መጨረሻ ውሃ መያዝ ይጀምራል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሰኔ ወር መጨረሻ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
ይህም ከጊቤ-1 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በሶስት እጥፍ እንደሚበልጥ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ እያካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከመጀመሪያው ጀምሮ ችግር የነበረበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የለውጡ አመራር ከመጣ ወዲህ ግንባታው በፍጥነት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የግንባታውን ሂደት የምክር ቤቱ አባላት በየጊዜው ሲጎበኙ እንደነበር አስታውሰው፤ ''አሁን ላይ የሚገኝበትን ደረጃ ማረጋገጥ ይቻላል'' ብለዋል።
''ግድቡ ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያወጣ ፕሮጀክት ነው''ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ አብሮ የመልማት እንጂ የሌሎች አገሮችን ጥቅም የመንካት ፍላጎት የሌላት መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ ሱዳንና ግብጽን የሚጠቅም ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የዲፕሎማሲ፣ የቴክኒክ፣ የውሃ ሙሌት፣ ገንዘብ የማሳባሰብና የተለያዩ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ እንደሚገኙ አመላክተዋል።
ፕሮጀክቱን ለማፋጠን ከለውጡ ወዲህ የአመራሮችና የኮንትራት ለውጥ መደረጉን ገልጸዋል።
እንደገና በማጥናት በአንድ ዓመት ተኩል ብቻ የግድቡ ዋና አካል 35 ሜትር ከፍታ ያለው ግንባታ መካሄዱን ገልጸው፤ የለውጡ አመራር እስኪመጣ 25 ሜትር ከፍታ ብቻ በዋናው የግድቡ አካል ላይ የተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ላይ ከዜሮ የመጀመር ያህል ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም ግድቡ በዚህ ዓመት በሰኔ ወር መጨረሻ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር ገልጸዋል።
''ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተጨማሪ 35 ሜትር ከፍታ በመጨመር 595 ሜትር ርዝመት ላይ ሲደርስ 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ወይም አሁን ከሚይዘው ከሶስት እጥፍ በላይ ውሃ ይይዛል'' ብለዋል።
የግድቡን ግንባታ በተመለከተ የተለያየ መሰረተ ቢስ ወሬ እንደሚናፈስ ገልጸው፤ ግንባታው ከሚናፈሰው መሰረተ ቢስ ወሬ በተቃራኒ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
''የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በሚካሄደው ድርድር ውስጥ ያሉትን ኢትዮጵያውንን መንግስት ያመሰግናል'' ብለዋል።
የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በ2003 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ነበር።