ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሠላማዊ መንገድ በድርድር የሚፈታ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሠላማዊ መንገድ በድርድር የሚፈታ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ። 

በዚህ ዙሪያ የሚነሱት ጉዳዮች ለውጊያ የሚያበቃ አንዳችም ምክንያት የላቸውም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ልዩ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር የተፈጠረው ክስተት ከምክር ቤቱ አባላት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ነው።

ለጉዳዩ መፍትሄ ለማበጀት መንግስት እየሰራ ያለው የዲፕሎማሲ ስራ ምን ይመስላል? የሚል ጥያቄ ተነስቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሰጡት ምላሽም ስለተፈጠረው ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋር ሰፊ ውይይት እያደረገ ነው ብለዋል።

መሰል ውይይቶች በቀጣይም እንደሚካሄዱና የሚነሱ ጉዳዮችን በሠላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት ጉዳዩን መፍታት የሚችሉትና መፍትሄም የሚገኘው በሠላማዊ መንገድ በድርድር ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል።

የድንበር ጉዳይ ለውጊያ ምክንያት ከሆነ ሱዳን ከግብጽ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ከፍተኛ ክርክር የሚነሳበት ቦታ እንዳለ አንስተዋል።

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ ለውጊያ የሚያበቃ ነገር የለውም ብለዋል።

በሱዳን በኩል ሚሊሻ ወደ አገራችን እየገባ ነው፣ ወደ መሬታችን እየገባችሁ ነው፣ ጉዳዩ በገላጋይ ዳኛ ይታይ የሚሉ ሃሳቦች እየተነሱ መሆናቸውንና ጥያቄዎቹም ተገቢ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና ጉዳዮቹ ጥይት ለመተኮስ የሚያደርሱ እንዳልሆኑና ችግሩን በድርድር ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

አገራቱ ተነጋግረው መግባባት ላይ የማይደርሱ ከሆነ የአፍሪካ ኅብረት ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ እንዲበጅለት የማድረግ ስራ እንዲያከናውን ኢትዮጵያ ፍላጎቷ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን ሕዝብ የመውጋት ፍላጎት የለውም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም በሱዳን መንግስት ላይ ውጊያ የመክፈት ፍላጎት የለውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።

የሱዳን ሕዝብ ለኢትዮጵያ ወንድም ሕዝብ ነው በማለትም በብዙ የታሪክ አጋጣሚዎች ለኢትዮጵያዊያን ባለውለታ እንደሆነ አውስተዋል።

የአገራቱ ሕዝቦች ለዘመናት በደምና በስጋ የተሳሰሩ አንድ ሕዝቦች መሆናቸውን በመግለጽ።

ኢትዮጵያን ከወንድሞቿ በማጣላት ትኩረቷን እንድትቀይር ለማድረግ የሚጥሩና ኢትዮጵያና ሱዳንን ለማዋጋት የሚደክሙ ኃይሎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ 'የእኛ ትኩረት አሁን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ነው፤ ከዛ ላይ ዓይናችንን አናነሳም" ነው ያሉት።

ከሱዳን ጋር ውጊያ እንደማያስፈልግና ጉዳዩ በመነጋገርና በመወያያት እንደሚፈታም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም