ቀጥታ፡

መንግስት የጣና ሃይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ1/2012(ኢዜአ) መንግስት የጣና ሃይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ በሰውና በማሽን እያደረገ ካለው ጊዜያዊ ጥረት ባሻገር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ከአውሮፓ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ማሽን ለመግዛት የድርድር ሂደት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ እያካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የእንቦጭ አረም በጣና ሃይቅ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።

ችግሩን ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጡ ባለመሆናቸው ውጤቱ የሚጠበቀውን ያህል አልሆነም እንዲያውም ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል።

''የችግሩም መነሻም ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጣ ደለል ዋነኛው ነው'' ብለዋል።

''ከጉና ተራራ ባለው ከፍተኛ የዝናብ መጠን የሚመጣው ጎርፍ የሚያጠቃው ፎገራን ሲሆን የፎገራን ለም መሬት አጥቦ የሚመጣው ጎርፍ በጣና ሀይቅ ላይ ደለል ይፈጥራል'' ብለዋል።  

''ጣና መጥቶ ለእንቦጭ አረም ምግብ የሚሆነውን ደለል ማስቀረት ካልተለቻለ ዘላቂ መፍትሄ አናመጣም ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። 

የክልሉ መንግስት በማሽንና በሰው ሃይል እንቦጭን ለመቀነሰ ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

''በቀጣይም በሰውና በማሽን የሚደረገውን ጥረት ባለማቋረጥ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ይሰራል'' ነው ያሉት።

''እስካሁን የተሞከሩ ማሽኖች ውጤታማ ስላልሆኑ የፌዴራል መንግስት ከአውሮፓ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የተሻለ ማሽን ለማምጣት እየተደራደረ ነው'' ብለዋል።

ይህም ሆኖ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም መፍትሔው የአካባቢ ጥበቃን ማጠናከር መሆኑን ጠቁመዋል።

''በአገር ደረጃ የተጀመረው የ5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ የእንቦጭ አረምን ለመከላከልና የአካባቢውን ነዋሪ ከጎርፍ አደጋ ስጋት ለመታደግ ወሳኝ ነው'' ብለዋል።

''ጣናን መታደግ ተገቢና አስፈላጊ ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ለማድረግ ሁሉም ደንን ማልማት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም