ቀጥታ፡

ኮቪድ-19 ካሳደረው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ባሻገር የአገሪቷ የወጪ ንግድ መሻሻል አሳይቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ ካሳደረው ተጽዕኖ ባሻገር የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ መሻሻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።

ባለፉት 10 ወራት ወደ ውጭ በተላኩት ቡና፣ አበባና ሌሎች ምርቶች የ13 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ልዩ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ እያካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድም ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ኮቪድ-19 በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ካሳደረው ተጽዕኖ ባሻገር የወጪ ንግዱ እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል።

ባለፉት 10 ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 667 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንና ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን በመግለጽ።

የዓለም ፍላጎትና የኢትዮጵያ አቅርቦት መጨመሩ በአንጻሩ ደግሞ ሌሎች አቅራቢ አገራት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ማቅረብ አለመቻላቸው ለዕድገቱ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

በኮሮና ሳቢያ በሌሎች አገራት የአበባ ምርት ሲጎዳ በተቃራኒው በኢትዮጵያ ጨምሯል፤ ባለፉት 10 ወራትም 440 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 84 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት።

ከስጋ ምርት የተገኘው 45 ሚሊዮን ዶላር ገቢም የ21 በመቶ ጭማሪ አለው ብለዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ባለው ከፍተኛ የስጋ ፍላጎት በአገር መሪዎች ደረጃ ጭምር ተጨማሪ ጥራት ያለው ስጋ እንዲቀርብ መጠየቁን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ወደ ውጭ ከተላከ የወርቅ ምርት 27 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፤ ይህም የ19 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።

ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ምርቶች በተለይ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ለዚሁ ግዥ ይውል የነበረው ወጪ ሌሎች ምርቶችን ለመግዛት እንዳስቻለም አክለዋል።

በአንጻሩ የኮሮና ቫይረስ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩንና የአገልግሎት ዘርፉም መጎዳቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተናግረዋል።

በቱሪዝም ዘርፍ የደረሰውን ተጽዕኖ ለማካካስ የእንጦጦና የአንድነት ፓርኮች እንዲሁም የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻን ልማት ከኮሮና በኋላ በማስጎብኘት ትልቅ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ካሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች በተጨማሪ እየተገነቡ ያሉት መስህቦች የዘርፉን ጉዳት ለማካካስ እንደሚረዱም ተናግረዋል።

በተመሳሳይም የቫይረሱ ወረርሽኝ በሬሚታንስ ላይ ቫይረሱ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም