ቀጥታ፡

ከግብርና ማግኘት የሚገባንን ሃብት ለማግኘት አቅማችንን አሟጠን መስራት ይኖርብናል

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1/2012 ( ኢዜአ)  ''ከግብርና ዘርፍ ማግኘት የሚገባንን ሃብት ለማግኘት አቅማችንን አሟጠን መስራት ይኖርብናል'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ እያካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

የግብርና ዘርፍ ስራዎችን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

በኩታ ገጠም የተጀመረውን የእርሻ ስራ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፤ ለአብነትም በአርሲ አካባቢ በኩታ ገጠም የተሰራው የእርሻ ስራ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጤፍ በማምረት የሚታወቁ የሸዋ አካባቢዎች አሁን በስፋት አቦካዶ ማምረት መጀመራቸው ገልጸው፤ አቦካዶ ከአመታት በኋላ የቡናን ያህል በወጪ ንግድ ገቢ የማስገኘት አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

አቦካዶ በኢትዮጵያ ምርት የሚሰጠው በከፍተኛ ደረጃ የሚፈለግበት ወቅት ላይ በመሆኑ ትልቅ የገበያ ዕድል እንዳለው ገልጸዋል።

ተክሉ ተራርቆ የሚተከል ስለሆነ በመሃሉ እንደ ሽንኩርትና ድንች ያሉ አትክልቶችን በማልማት ምርትን ማሳደግ የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።

አቦካዶ በአንድ ሄክታር ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊዮን ብር ሊገኝበት እንደሚችልም ጠቁመዋል።

''በዘንድሮው የአምስት ቢሊዮን ችግኝ የመትከል አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ውስጥ አብዛኛው ዛፍ የፍራፍሬ ተክል እንዲሆን የተፈለገውም ችግኝ መትከልና አካባቢን መንከባከብ ብቻ ሳይሆን በዚያም ውስጥ መብላትና መሸጥ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ነው'' ብለዋል።

በቆላማ ቦታዎች እርሻዎች ዘንድሮ 20 ሺህ ያህል ሄክታር በማልማት በሄክታር በአማካኝ 42 ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል። በዚህም ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ሊገኝ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህ ስራ በሚቀጥለው አመት የሚስፋፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘንድሮ ከ10 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ በማስገባት ምርት እንዳይቀንስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

14 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በዚህ አመት ለማስገባት ዕቅድ መያዙን ገልጸው፤ ''ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና ከወደብ ሎጂስቲክ ውስንነት ጋር ተያይዞ በተወሰነ ደረጃ ችግር የገጠመ ቢሆንም እስካሁን 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ክልሎች ጋር ደርሷል'' ብለዋል።

''1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት ውስጥ የሚገባ ይሆናል'' ነው ያሉት።

ይህንን ለማፋጠን የሎጂስቲክ ስርዓቱን ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ወትሮው ሁሉ የምርጥ ዘር እጥረት ማጋጠሙ እንደማይቀር ጠቁመው፤ ሰፋፊ እርሻዎች ላይ የምርጥ ዘር ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

የአረምና የተባይ መከላከያ ኬሚካል መዘጋጀቱን ገልጸው፤ የማሳ ዝግጅትም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በነዚህ ዝግጅቶች መሰረት ከግብርና ዘርፍ ማግኘት የሚቻለውን ሃብት ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

መንግስት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሃብት መድቦ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም