በምእራብ ወለጋ የቡና ጥራት ማሻሻል እያሳየ መምጣቱን ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በምእራብ ወለጋ የቡና ጥራት ማሻሻል እያሳየ መምጣቱን ተገለፀ
ነቀምቴ ሰኔ 29/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን የቡና ጥራትን ለማሻሻል በተሰሩ ሥራዎች ውጤት መገኘቱን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡
አርሶ አደሮች ደግሞ ከዘርፉ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ገልፀዋል ።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ በዳሣ ኦልጅራ እንደገለፁት የአርሶ አደሩን የቡና ምርት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በግብርና ባለሙያዎች የታገዘ ተከታታይነት ያለው የሙያ ድጋፍ እየተደረገ ነው ።
ድጋፉ በቡና ለቀማና አደራረቁ ላይ ለውጥ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡
አርሶ አደሩ በለቀማ ወቅት የበሰለ ቡና እንዲለቀምና በአልጋ እና በሲሚንቶ በተሰራ ቦታ ላይ እንዲያደርቅ በማድረግ በገበያ ላይ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
የቡና ጥራትን ለማሻሻል ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ ያረጁ የቡና ዛፎችን መጎንደልና መንቀል ነው ያሉት አቶ በደሣ በዚህ ዓመት 10 ሺህ 490 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘውን ቡና የመጎንደልና ያረጁትን የመንቀል ስራዎች መሠራታቸውን አስረድተዋል ፡፡
የቡና ጥራትን ለማሻሻል በተከናወነው ሥራ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንዳንድ የዞኑ አርሶ አደሮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ፡፡
ከዞኑ አርሶ አደሮች መካከል የሆማ ወረዳ የሆማ ከተማ ነዋሪ አርሶ አደር ግዛው ደምሴ በሰጡት አስተያየት የግብርና ባለሙያዎች በሚያደርጉላቸው የሙያ ድጋፍ በመታገዝ ቀይ ቡና ብቻ በመሰብሰብና በአልጋና በሲሚንቶ በተለቀለቀ ቦታ ላይ በማድረቅ ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ተናረዋል፡፡
በዘንድሮው የምርት ዘመን ለጥራት ትኩረት ሰጥተው መስራት በመጀመራቸው የሰበሰቡትን 96 ኩንታል የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ አቅርበው ቀደም አንዱን ኪሎ ግራም ቅሽር ቡና በ70 ብር ሒሳብ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አርሶ አደር አሊ ናዶ በበኩላቸው 90 ኩንታል የቡና ምርት በመሰብሰብ በአካባቢያቸው ገበያ አንዱን ኪሎ ግራም ጀንፈል ቡና ከ20 ብር ወደ 33 ብር ከፍ አድርገው ለመሸጥ ጥራቱን አስተዋፅኦ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል ።
ቀደም ሲል የበሰለውንና ያልበሰለውን በማደባለቅ በሚሰበስቡበት ወቅት የአንድ ኪሎ ጀንፈል ቡና ዋጋ ከ18 እስከ 20 ብር ነበር ያሉት አርሶ አደሮቹ አሁን ለቡና ጥራቱ ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው እስከ 33 ብር መሸጣቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዞኑ የቡና ልማት በጥራትም ሆነ በብዛት ለማሳደግ በዘንድሮው ክረምት 141 ነጥብ 3 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ለመትከል ጉድጓዶች ተዘጋጅተዋል ።
በተከላው 103 ሺህ 305 የዞኑ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል ።
በምዕራብ ወለጋ ዞን 451 ሺህ 666 ሄክታር መሬት በቡና ተክል እየለማ ሲሆን ዘንድሮ 45 ሺህ ቶን ቡና መሰብሰብ እንደተቻለ ከዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡