ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ2 ሺህ አለፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 20 ሲያልፍ፤ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 3 መቶ ተሻግሯል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 20 ደርሷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) በሽታ ምላሽ አሰጣጥን አስመልክቶ በሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 6 ሺህ 92 የላብራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 86 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።

በዜግነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ተገልጿል።

ዛሬ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ በአንድ ቀን የተደረገ ከፍተኛው የላብራቶሪ ምርመራ ነው።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት ያላቸውንና የውጭ የጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች መረጃን አላካተተም።

ከሞቱት ሰዎች መካከል ስድስቱ ከአዲስ አበባ ሲሆኑ አንዱ ከኦሮሚያ ክልል ነው።

በአዲስ አበባ ከሞቱት መካከል የ34 ዓመት ሴት፣ የ65 ዓመት ሴት እና የ56 ዓመት ወንድ በህክምና ማዕከል ህክምና ሲደረግላቸው የነበሩ መሆናቸው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከሞቱት ውስጥ የ33 ዓመት ሴት፣ የ26 ዓመት ሴት እና የ55 ዓመት ወንድ በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል የሞተው ሰው ደግሞ የ36 ዓመት ወንድ ሲሆን በተደረገው የአስክሬን ምርመራ የሞቱ ምክንያት በቫይረሱ መሆኑ ታውቋል።

ዛሬ የተገለጸው የሞቾች ቁጥር በአንድ ቀን የተመዘገበው ከፍተኛው የሞት ቁጥር ሲሆን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 27 ደርሷል።

በአሁኑ ሰአት በጸና የታመሙ 32 ሰዎችም ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም