ቀጥታ፡

ተጨማሪ 86 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ የ7 ሰዎችም ሕይወት አልፏል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30/2012(ኢዜአ) በኢትዮጰያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 6092 የላብራቶሪ ምርመራ 86 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡

በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2ሺህ 20 ደርሷል፡፡

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ 51 ወንድና 35 ሴት እንዲሁም የዕድሜ ክልላቸው ከ7 እስክ 82 አመት እንደሆነ ታውቋል ።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 66 ሰዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣ 7 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 7 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 4 ሰዎች ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፣ 1 ሰው ከአማራ ክልል እንዲሁም 1 ሰው ከድሬደዋ ከተማ አስተዳዳር እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ላይ እያለች በሰላም እንደተገላገለች የተገለጸችው እናትን ጨምሮ ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ የ7 ሰዎች ህይወት አልፏል።

ከእነዚህ መካከል አራቱ በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው፣ ሶስቱ ደግሞ በሕክምና ማዕከል በሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ መሆናቸው ታውቋሏ።

በዚህም አጠቃላይ በአገራችን በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 27 ደርሷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ በኩል በትላንትናው ዕለት 63 ሰዎች ( 46ቱ ከአዲስ አበባ፣ 13ቱ ከሱማሌ ክልል፣ 3 ከኦሮሚያ ክልልና 1 ከአማራ ክልል ) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 344 መድረሱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 7 ቀናት ብቻ 848 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ እንዲሁም 16 ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉ መረጋገጡን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ነገር ግን በኅብረተሰቡ ዘንድ በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ የመከላከያ ዘዴዎችን ከመተግበር አኳያ እጅግ የበዙ ክፍተቶች መኖራቸውን መስተዋሉን ገልጿል።

ስለሆነም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ክልሎች፣ የከተማ አስዳደሮች እና የሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ሌሎች አካላት የበሽታው ሥርጭት ተስፋፍቶ ከአቅም በላይ ከመድረሱ እና ለከፋ ችግር ከመዳረጋችን በፊት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ከምንጊዜውም በላይ ኅብረተሰቡን ባማከለ እና ባሳተፈ መልኩ አስፈላጊውን የመከላከል ሥራ እንዲተገብሩ በአፅንኦት አሳስበዋል።

እስካሁን በአገራችን አጠቃላይ 142 ሺህ 960 የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም