የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች በከተሞች አካባቢ ያሰፈሯቸውን ወታደሮች ለማንሳት ስምምነት ላይ ደረሱ

19
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በከተሞች አካባቢ ያሰፈሯቸውን ወታደሮች ወደ ሌሎች ስፍራዎች ለማንቀሳቀስ ተስማሙ። ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና የቀድሞው ምክትላቸው ሬይክ ማቻር በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አደራዳሪነት በሱዳን ካርቱም የቀጠሉትን የፊት ለፊት ውይይትን ተከትሎ ሁለቱ አካላት ትናንት በካርቱም አዲስ ስምምነት ተፈራርመዋል። የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አል በሽር በተገኙበት የተደረሰው ይህ አዲስ ስምምነት ለሰብአዊ እርዳታ እንቅስቃሴዎች አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል ተስፋን አጭሯል። ከዚህ ቀደም ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረማቸውን የተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ስምምነቱ ሁለቱ ወገኖች ሲቪል ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ያሰፈሯቸውን ወታደሮች ማንሳት፣ ወታደሮቻቸውን በመቀላቀል በአንድ እዝ ውስጥ ለማሰባሰብ ቀነ-ገደብ ማስቀመጥንና የጦር ሰራዊቱ የሚሰፈርበትን ቦታ መወሰንን የሚያካትት ነው። ተፋላሚ ወገኖቹ ምርኮኞችን በአስቸኳይ ለመልቀቅ የተስማሙ ሲሆን ተግባራዊነቱን የሚከታተል አንድ የጋራ የፀጥታ ኮሚቴ ለማቋቋምም  ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አል-ዲርዲር መሐመድ አህመድ “በሀገሪቱ መረጋጋትን እውን ማድረግ እንዲቻል ደቡብ ሱዳናዊያን ታጣቂዎች ትጥቃቸውን መፍታት ያለባቸው ወሳኝ ወቅት አሁን ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በፀጥታ ጉዳዮች ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በቅድሚያ በከተሞች አካባቢ ያሰፈሯቸውን ወታደሮች ወደሌሎች ስፍራዎች ያንቀሳቅሳሉ። በቤተ-ክርስቲያናት፣ መንደሮች፣ ትምህርት ቤቶችና መጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ ምንም ዓይነት ወታደራዊ አንቅስቃሴ እንዳይደረግ በስምምነቱ ተደንግጓል። ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማቻር በስልጣን መጋራት ጉዳዮች ዙሪያ የሚያካሄዱትን ድርድር ከወዲሁ መጀመራቸውን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል። አዲሱ ስምምነት በስልጣን መጋራት ጉዳዮች ላይ የሚካሄደው ድርድር የተሳካ አንዲሆን መልካም እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል። በስልጣን መጋራት ላይ የሚካሄደው ድርድር በኡጋንዳ ርእሰ መዲና ካምፓላ አንደሚቀጥል የተነገረ ሲሆን በውይይቱም የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የሱዳን አቻቸው ኡመር ሀሰን አልበሽርና የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር አንደዚሁም ሬክ ማቻር ይገኛሉ ተብሏል። ላለፉት አራት ዓመታት በደቡብ ሱዳን የተካሄደው የእርስ በእርስ ግጭት ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈ ከመሆኑም በላይ አራት ሚሊዮን ዜጎችን አፈናቅሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም