ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመደራደር አቅሟን ልታጠናክር እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመደራደር አቅሟን ልታጠናክር እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ
ባህርዳር፣ ግንቦት 30/2012 (ኢዚአ) ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን በፍትሃዊነትና እኩልነት መርህ በዘላቂነት ተጠቃሚ ለመሆን ዓለም አቀፍ የመደራደር አቅሟን ልታጠናክር እንደሚገባ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተናገሩ።
የአማራ መገናኛ ብዙሃን ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በህዳሴ ግድብና በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዚ ፈረደ ዲፕሎማሲው በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጹሁፍ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ህዝቦቿን ከድህነት ለማላቀቅ የውሃ ሃብቷን የመጠቀም መብቷ በማንኛውም መመዘኛ የተጠበቀ ነው።
ኢትዮጵያ በህዝቦቾ ተሳትፎ እየገነባች ያለውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለማስቆምና የዲፕሎማሲ የበላይነቱን ለማግኘት ግብጽ ያለመሰልቸት እየተንቀሳቀሰች ነው ብለዋል።
በዚህም የተከፋፈለች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ጥረት እያደረገች መሆኗን መንግስት ተገንዝቦ ውስጣዊ አንድነቷ የጠነከረች ሀገር ለመፍጠር መስራት እንዳለባት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአሁኑን የዓለምን የለውጥ ሂደት በመቃኘት ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አቅሟን አጠናክራ በድርድሩ አሸናፊ የሚያደርጋትን ሃሳብ በማቅረብ ሁኔታውን መቀየር አለባት።
"ለዚህም ለአፍሪካ ጥያቄ አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲኖር መስራት አለባት "ያሉት ምሁሩ በፍትሃዊ መርህ ላይ የተመሰረተ ጥቅምን የማስጠበቅ ሚና አጉልቶ ማሳየት እንደሚገባም አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ዘውዱ መንገሻ በበኩላቸው ዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ህግና የአባይ ወንዝ የሚል ጽሁፍ ለተወያዮች አቅርበዋል።
በዚህ ጽሁፋቸው እንዳሉት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሀገራት ፍፁም የሆነ የግዛት ሉዓላዊነት፣ ገደብ ያለበት የተፋሰስ ሀገራት ሉዓላዊነት፣ አንድነትና እኩል ተጠቃሚነትን ማጎልበት የሚሉ ዓለም አቀፍ ህጎች አሉ።
መሰረታዊ ዓለም አቀፍ የልማድ ህጎች ድንበር ተሻጋሪ ውሃን በፍትሃዊነትና እኩልነት የመጠቀም መብትና በተፋሰሱ ሀገራት ጉልህ ጉዳት አለማድረስ ግዴታን እንደሚጥልም አስረድተዋል።
"የናይል ተፋሰስ ሀገራትም የአለም አቀፍ ህግን በማክበር ያለንን የውሃ ሃብት ድርሻ በፍትሃዊና በእኩልነት ላይ ተመስርቶ ለመጠቀም በጋራ ተግባብተውና ተባብረው ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።
የሚካሄዱ ድርድሮችም መጪውን ትውልድ በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብቱን እንዳይገድብ ጥንቃቄ ማድረግና አዳዲስ የመደራደሪያ ሃሳቦችን ማፍለቅ ከተደራዳሪዎች እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን በየጊዜው በተሳሳተ መልኩ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለግብፆች የልብ ልብ እንዲኖራቸው ማድረጉን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ናቸው።
ለዚህም በውሃ ሃብቱ የበለጠ ተጠቃሚ መሆንን የድርድር የበላይነቱን ለማስፈን ውስጣዊ አንድነትን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ እንደገለጹት ስለ አባይ የሚደረጉ ክርክሮችን ለግብፅ ህዝብ በፈረንሳይኛና አረብኛ ቋንቋዎች ጭምር በማስተላለፍ ሀቁን ለህዝቡ ማስረዳት ይገባል።
ኢትዮጵያ በመርህ ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንድትሆንም ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በአባይ ላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በፓናል ውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የተውጣጡ አካላት ተሳትፈዋል።