ቀጥታ፡

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ 200 ለሚሆኑ ለተቸገሩ ወገኖች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አምቦ፣ ግንቦት 30/2012 (ኢዜአ) የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ወረርሽን ምክንያት ለተቸገሩ የጉደር ከተማ የአካል ጉዳተኞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 200 ወገኖች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

በጉደር ከተማ ትናንት የተደረገው ድጋፍ  በነፍስ ወከፍ 70 ኪሎ ግራም የስንዴ፣ የጤፍ ዱቄትና ሩዝ እንዲሁም 200 ኪሎ ግራም የምግብ ጨውና የንፅህና መጠበቂያ ሳሙና ነው።

በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ በዚህ በአስቸጋሪ ጊዜ  ማህበረሰቡ እርስ በእርስ በመደጋገፍና በመረዳዳት መሻገር አለብን ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ቀደም ብሎም ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና የምግብ እህል  እንዲሁም አልባሳትን በአምቦ ከተማ ለሚገኙ ከ1ሺህ በላይ የተቸገሩ ወገኖች ማከፋፈሉን አውስተዋል፡፡


ለለይቶ ማቆያና ለህክምና አገልግሎት እንዲውል በዩኒቨርሲቲው የአዋሮ ካምፓስን ከማዘጋጀት ጀምሮ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን ብለዋል።


የኮሮና  መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢና የጉደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፊጣ ረጋሳ  ዩኒቨርሲቲው ላበረከተው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ቶለሺ ባልቻ በወረርሽኙ ምክንያት እንደልብ ወጥተው መስራት ባለመቻላቸው ከነልጆቻቸው ለችግር በተጋለጡበት በዚህ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ስለደረሰላቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም