ቀጥታ፡

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ያሰለጠናቸው 2 ሺህ 260 የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላትን አስመረቀ

ሀዋሳ፣ ግንቦት 30/2012(ኢዜአ) የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ በብላቴ ጊዜያዊ ማሰልጠኛ ያሰለጠናቸው 2ሺህ 260 የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት አስመረቀ።

በማሰልጠኛው ትናንት በተካሄደው የምረቃ ስነስርዓት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተደድር አቶ ርስቱ ይርዳው ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማት ጉዞ ለማሳካት ወሳኙ ሠላም መሆኑን ገልጸዋል።

ሠላምን ለማረጋገጥ የፖሊስ ኃይሉ እየተጫወቱ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።


የአሁኑ ተመራቂዎችም ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ በስልጠና ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ በፍጹም ቅንነትና ሀገር ወዳድ መንፈስ ወደተግባር በመለወጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።


የክልሉ ፖሊስ  ኮሚሽነር ነቢዩ ኢሳያስ  በበኩላቸው የክልሉን ሠላምና ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ የተጀመረውን ሪፎርም በፖሊሳዊ ሳይንሳ በማስደገፍ  የአቅም ግንባታ ስልጠና ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

የአሁኑ የስድስተኛው ዙር ተመራቂዎች  ላለፉት አራት ወራት የተሰጣቸውን የንድፍና የተግባር ስልጠና ያጠናቀቁ መሆናቸው  ተመልክቷል።


ኮሌጁ  እስካሁን ከአምስት ሺህ 500 በላይ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላትን ማስመረቁም ተወስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም