ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ማስጠበቅ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው --- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ማስጠበቅ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው --- ምሁራን
ነቀምቴ ግንቦት 29/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን በማስጠበቅ ዘላቂ ልማቷን ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያ 86 በመቶው የናይልን የውሃ ሀብት እያመነጨችና ለም አፈሯን ታጥቦ እየሔደ ለዘመናት የበይ ተመልካች መሆኗ ሊቆም እንደሚገባው ምሁራኑ ገልፀዋል ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን መካከል የግምቢ ካምፓስ የሕብረተሰብ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ገለታ ገመቹ እንዳሉት የአባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተፈጥሮ ሀብት በመሆኑ የባለቤትነት መብታቸው ተከብሮ ለልማት ሊጠቀሙበት ይገባል ።
የተፈጥሮ ሀብቱ ጥቅም ላይ ለማዋል ደግሞ መላው የአገሪቱ ህዝቦች ዘር፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድባቸው አንድነታቸውን አጠናክረው የግድቡን ግንባታ ከዳር ሊያደርሱት እንደሚገባ አሳስበዋል ።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን የሚከለክል ዓለም አቀፍ ሕግ የለም ያሉት ምሁሩ የታችኞቹን ተፋሰሱ አገሮችን በማይጎዳ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል ተገቢም ፍትሃዊም ነው ብለዋል ።
በአባይ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥ በአንድ በኩል ግንባታውን ማፋጠን በሌላ በኩል ደግሞ የዲፕሎማሲ ስራውን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁሩ ጠቁመዋል ።
የግድቡ ግንባታ በማጠናቀቅ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ማዋል ለነገ የሚባል አጀንዳ ባለመሆኑ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንረባረብ ምሁሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።
ሌላው የዩኒቨርሲቲው የሕብረተሰብ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍል አስተባባሪ መምህር ሙሉጌታ ላሜሳ በበኩላቸው ድንበር ተሸጋሪ ወንዞች የሚተዳደሩበት ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ በመኖሩ የታችኞቹ ብቻ ሣይሆን የላይኞቹ ተፋሰስ አገሮችም በሌሎች የጎላ ተፅዕኖ ሳያስከትሉ የመጠቀም መብት አላቸው ብለዋል ።
ግብፅ እንደ ሕግ ማዕቀፍ አድርጋ የምትጠቀመው በ1929 ኢትዮጵያን ሳያካትት የተደረገው የቅኝ ግዛት ስምምነት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በ1959 በግብፅና በሱዳን መካከል የተደረገው ስምምነትም ቢሆን የላይኛው ተፋሰስ አገሮችን ሳያካትት ግብፅንና ሱዳንን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግና ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን አስረድተዋል ።
በመሆኑም ሌሎችን ሳንጎዳ በውኃ ሃብታችን መጠቀም ህጋዊና ተገቢ በመሆኑ ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የዲፕሎማሲ ሥራችንን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል ።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በአባይ ጉዳይ ላይ አንድነታቸውን በማጠናከር ለአገር ጥቅም ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል ።
የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ አስተዳደርና የፖሊሲ ጥናት መምህር ዶክተር ቀዲዳ ሶንቶ እንዳሉት ደግሞ የአባይ ጉዳይ የግብፅና የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የተፋሰስ አገራት ጉዳይ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት በስምምነት እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋግጥ አብረው ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም ።