ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን የሕዳሴውን ግድብ አስመልክቶ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ጭምር መዘገብ እንዳለባቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በውጭው ዓለም ያለውን ብዥታ ለማጥራት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ተጠቅመው በሰፊው መዘገብ እንዳለባቸው ተገለጸ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪካ ጉዳይ ተንታኝ፣ ፀሐፊና ተመራማሪዎች እንዳሉት፣ ስለሕዳሴው ግድብ በዓለም አቀፍና በግብፅ ሕዝብ ላይ ያለውን ብዥታ ለማጥራት መገናኛ ብዙሃኑ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ጭምር ተጠቅመው መዘገብ አለባቸው።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ የሆኑት አቶ አንዋር ኢብራሂም ለኢዜአ እንዳሉት በግድቡ ላይ ያለውን እውነታ ለዓለም ማኅበረሰብ በሚገባ ለማሳወቅ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዓለም አቀፍ የሆኑ ቋንቋዎችን በመጠቀም ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።

ዓለም አቀፍ በሆኑ ቋንቋዎች መሥራት የሚያስፈልገው የግብፅ ሕዝብና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን እውነታ በአግባቡ እንዲረዱ ያደርጋል።

"ከዕለት ተዕለት የዘገባ ሥራዎች በተጨማሪ በግድቡ ዙሪያ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ዓለም አቀፍ በሆኑ ቋንቋዎች በማዘጋጀት ያለውን እውነታ ማሳወቅ ይገባል" ብለዋል።

የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየሰሯቸው ያሉት ሥራዎች የሚበረታቱ ቢሆንም ከወቅታዊ የግብፅ እንቅስቃሴ አንጻር ይበልጥ መሥራት እንደሚገባም አቶ አንዋር አሳስበዋል።

በዓባይ ጉዳይ የሚሰሩና ድርድር የሚያደርጉ የሥራ ኃላፊዎችም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ጭምር ተጠቅመው በግድቡ ላይ የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነት አቋም ማሳወቅ አለባቸው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ፀሐፊና ተንታኝ የሆኑት አቶ ሙሳ ሼኮ በበኩላቸው በግብፅ በኩል የሕዳሴውን ግድብ አስመልክቶ ለሚወጣ እያንዳንዱ ዜናና መረጃ ዓለም አቀፍ በሆኑ ቋንቋዎች ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩልም ከግድቡ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በተለያዩ የዓለም ቋንቋዎች በማዘጋጀት እውነታው ለዓለም ማኅበረሰብ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የተፋሰሱን አገራት ጥቅም ጭምር ለማስከበር እየሰራች ስለመሆኗ እና ሌሎች ሀገራት ጥቅማቸውን በማይነካ መልኩ የራሳቸውን ድርሻ እንዲያገኙ እያደረገች መሆኗን በአግባቡ ማሳወቅ እንዳለባትም አስገንዝበዋል።

በተለይ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ቋንቋ በሆነው ዐረብኛ ተከታታይ የዘገባ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ አቶ ሙሳ አሳስበዋል።

"በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተለያዩ ዜዴዎችን ተጠቅሞ ለዓለም ህዝብ ማሳወቅ ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት አቶ አብዱሹኩር አብዱሰመድ ናቸው።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ከአንዳንድ የግብፅ ሚዲያዎች የሚወጡ መረጃዎችን ትክክለኛነት ሳያረጋግጡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም