ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ 40 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የሕክምና ቁሶችን ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዙ 40 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የሕክምና ቁሶችን ለጤና ሚኒስቴር በድጋፍ አበረከተ።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በቀን አንድ ዶላር ለወገኖቻቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት የተቋቋመ ነው።

ፈንዱ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ በዋናነት ቫይረሱን ለመከላከል ግንባር ቀደም ሆነው ለተሰለፉ የጤና ባለሙያዎች የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

ከቫይረሱ መከላከያ ግብዓቶች በተጨማሪ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎችን ለማከም የሚረዱ የህክምና ቁሶች በድጋፉ ውስጥ መካተታቸው ተመልክቷል።

ድጋፉን የኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ ለጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ አስረክበዋል።

ሊቀመንበሩ በዚህን ወቅት እንዳሉት፣ ትረስት ፈንዱ እስካሁን ባለው ሂደት 6 ሚሊዮን ዶላር አሰባስቧል።

ከዚህም ውስጥ 1 ሚሊዮን አንድ መቶ ሰባ ሺህ ዶላር በማውጣት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ቁሶችን ገዝቶ ድጋፍ ማድረጉን ነው የተናገሩት።

ቀሪውን የተሰበሰበ ገንዘብ ውሃና ሌሎች የዜጎች መሰረታዊ ችግሮችን በሚቀርፉ ፕሮጀክቶች ላይ ለማዋል ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ለተጠቀሰው ዓላማ የሚውሉ 21 ፕሮጀክቶች ቀርበው አምስቱን በቅርቡ ሥራ ለማስጀመር የስምምነት ፊርማ መደረጉን ነው የገለጹት።

እንደ አቶ ዛፉ ገለጻ ቀሪ 16 ፕሮጀክቶች አስፈላጊው ማጣራት ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ውይዘሮ ብርቱካን አያና በበኩላቸው የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት የዲያስፖራውን ድጋፍ የሚያስተባብር ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም ዲያስፖራው ለቀረበለት ጥሪ  በጎ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን አስታውሰው፣ ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ለተደረገ ድጋፍም በሚኒስቴሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም ዲያስፖራው ለአገሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረቡት ሚኒስቴር ዴኤታዋ መንግስት የሚጠበቅበትን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

"የገጠመን የጤና ቀውስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድንገት የተከሰተ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩ የሚፈታው በተናጥል ሳይሆን በመተጋጋዝ ነው" ያሉት ደግሞ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ናቸው።

"የተደረገልን ድጋፍ የበርካታ ዜጎቻችንን ህይወት እንድንታደግ ያግዘናል" ሲሉም አክለው ገልጸዋል።

"ድጋፉ በተለይ ለጤና ባለሙያዎች የሚውል በመሆኑ ቫይረሱን ከመከላከል አንጻር የሚያበረክተው ሚና ድርብ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም