ቀጥታ፡

ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ማንኛውም ጉዳይ ላይ እጇን እንደማታስገባ የአገሪቱ አምባሳደር ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2012 (ኢዜአ) ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ማንኛውም ጉዳይ ላይ እጇን እንደማታስገባ አምባሳደር ጄምስ ሞርጋን ዛሬ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አምባሳደሩን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

አምባሳደር ሞርጋን በውይይቱ ወቅት "ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ በማንኛውም ጉዳይ ላይ እጇን አታስገባም" ብለዋል።

ሰሞኑን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች የተለቀቀውና ''ደቡብ ሱዳን በግዛቷ ለግብፅ መንግሥት የወታደራዊ ካምፕ ግንባታ የሚያገለግል ቦታ ለመስጠት ከግብፅ ጋር ተስማምታለች ''በሚል የተናፈሰው ዜና መሠረተ ቢስ ነው በማለት ገልጸዋል።

መንግሥታቸው ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቶ ጁባ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲደርስ ማድረጉን ገልጸው፤ ኤምባሲያቸውም በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱን ተናግረዋል።

ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ራሷን እንድትችልና የበለጸገች እንዲሁም የሕዝቦቿን ተጠቃሚነት ያረጋገጠች አገር እንድትሆን ኢትዮጵያ የጎላ ድጋፍ  ማበርከቷን አምባሳደር ሞርጋን አብራርተዋል።

''የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ሕዝቦች በሁለት አገር ውስጥ የሚኖሩና በርካታ ነገሮችን የሚጋሩ አንድ ሕዝቦች ናቸው'' ብለዋል።

''ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በመጠቀም የመልማት መብቷን ደቡብ ሱዳን በጽኑ ትደግፋለች፤ ፍላጎቷንም ታከብራለች ''ሲሉም ተናግረዋል።

አገሮቹ በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትብብር እየሰሩ ባለበት ወቅት የተለየ ተልዕኮ ያላቸው አካላት የሚያደርጉትን ያልተገባ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ  ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ለመመከት እንደምትሰራ  አስታውቀዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በቀጠናው የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት ጉልህ ሚና የሚጫወትና  ተነሳሽነትን ስለሚፈጥር በአገራቸው ሕዝብና መንግሥት በኩል ሙሉ ድጋፍ ያለው ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት የሁሉንም አገር ጥቅም ባማከለና የሕዝቦቿን ፍላጎት ባጣጣመ መልኩ በውይይት መፈታት እንዳለበት አገራቸው እንደምታምን አምባሳደር ሞርጋን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ  ለአገራቸው የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ለመከላከያ  ላደረገችው ቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

አቶ ገዱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀውን ዜና ትክክል ነው ብላ እንዳልወሰደችው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ዋጋ ትሰጣለች ያሉት ሚኒስትሩ፤ በናይል ወንዝ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያን የምትቃወምበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌላት በውል  እንገነዘባለን  ብለዋቸዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ወንድሞቿ ጋር በጋራና በትብብር የመልማት በመርህ ላይ የተመሰረተና ለዘመናት የዘለቀ አቋሟን በማጠናከር ከደቡብ ሱዳን ጋር በመሠረተ ልማት ለማስተሳሰር ትሰራለችም ብለዋል።

ደቡብ ሱዳን የተረጋጋችና የሕዝቦቿን ጥቅም ያረጋገጠች አገር እንድትሆን ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምታጠናክር  አቶ ገዱ በዚህ ወቅት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም