ቀጥታ፡

ሠራዊቱ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ግዳጆችን በብቃት እንደተወጣው ሁሉ ኮቪድ -19ን ለመከላከል ግንባር ቀደም ሆኖ ተሰልፏል... ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2012(ኢዜአ) መኮንን ሠራዊቱ ዛሬም እንደ ትናንቱ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ግዳጆችን በብቃት እንደተወጣው ሁሉ፤ አሁንም ኮቪድ -19ን ለመከላከል ግንባር ቀደም ሆኖ ተሰልፏል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አመራሮችና ሲቪል ሰራተኞች በኮቪድ-19 የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ያሰባሰቡትን ከ50 ሚሊዮን 876 ሺህ ብር ለብሔራዊ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴው ዛሬ አስረክበዋል።

ሠራዊቱ ለአገርና ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ዳር ድንበሩን በማስከበር መደበኛ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የአገሩን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባለፈ በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች እየተሳተፈ መሆኑም ይታወቃል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት እስካለፈው ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድና በተለያዩ ዘርፎች አስተዋጽኦ አድርጓል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በድጋፉ ርክክቡ ላይ እንዳሉት ኮቪድ-19ን ለመከላከል የዓለም የጤና ድርጅትና የጤና ሚኒስቴር ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ዝግጅት ተደርጓል።

በዚህ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የጸጥታ አካላት በተለያዩ ማኅበራዊ ዘርፎች ኅብረተሰቡን እያገለገሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሠራዊቱ ዛሬም እንደ ትናንቱ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ግዳጆችን በብቃት እንደተወጣው ሁሉ፤ አሁንም ኮቪድ -19ን ለመከላከል ግንባር ቀደም ሆኖ ተሰልፏል ነው ያሉት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ "ሠራዊቱ ጉልበቱን፤ዕውቀቱንና ገንዘቡን ሳይሰስት የሚሰጥ የአገር ደጀን ነው" ብለዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ በበኩላቸው የሠራዊቱ አመራርና ሲቪል ሠራተኞች ከመደበኛ ግዳጃቸው በተጨማሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሠራዊቱ የተለያዩ ዕዞች በራሳቸው ተነሳሽነት 4 ሚሊዮን 785 ሺህ ብር በማዋጣት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ሠራዊቱ ድጋፉን ያደረገው ''ለክፉ ጊዜ ከተቀመጠው ሃብት ሳይሆን፤ ሁልጊዜም ካለው ማካፈል ልማዱ ስለሆነ ነው'' ብለዋል።

በመሆኑም የሠራዊቱ አመራርና ሲቪል ሠራተኞች ያደረጉት ድጋፍ የላቀ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ኅብረተሰቡ ''እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚሉ አካላትን በጥብቅ መሞገት ይገባዋል'' በማለት፤ ወቅቱ ትብብርና መተሳሰብን የሚጠይቅ በመሆኑ ከሴራ ይልቅ ለእውነት መቆምና መታገል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም