የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሲሚንቶ እንዲያከፋፍሉ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2012(ኢዜአ) በሲሚንቶ ምርት ላይ የታየውን ችግር ለማቃለል አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና 12 አከፋፋዮች ብቻ ምርቱን እንዲያከፋፍሉ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ወሰነ፡፡

የመሸጫ ዋጋው መንግሥት በሚያወጣው የዋጋ ተመን ብቻ እንደሚከፋፈልም ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ በሲሚንቶ ምርት ላይ የተከሰተውን እጥረትና የዋጋ ንረትን ለመቀነስ በተወሰደው እርምጃ ላይ ዛሬ ለኢዜአ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን የሲሚንቶ ዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የስርጭት መጠኑን ወደነበረበት ለመመለስ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በዚህም መሠረት ምርቱን ከፋብሪካዎች የሚረከቡ አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና 12 በፋብሪካዎቹ በሚለዩ አከፋፋዮች  ብቻ ምርቱን ይከፋፈሉ ብለዋል፡፡  

ድርጅቶቹም አምባሰል የንግድ ሥራዎች ፣ ወንዶ ንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያ፣ ቢፍቱ አዱኛ ቢዝነስ ሼር ካምፓኒ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቶቹ በየዕለቱ 340ሺህ 238 ኩንታል ሲሚንቶ ከፋብሪካዎች በመረከብ እንደሚያከፋፍሉም  አቶ ወንድሙ አስታውቀዋል፡፡

ሲሚንቶ እንዲያከፋፍሉ የተመረጡት ድርጅቶችና አከፋፋዮችም ምርቱን ለመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ለግል አከፋፋዮች በእኩል መጠን ያከፋፍላሉ ብለዋል፡፡

ምርቱ መንግሥት በሚወስነው የዋጋ መጠን ብቻ እንደሚከፋፈልም  ኃላፊው ተናግረዋል፡፡  

የምርቱ የመሸጫ ዋጋና የትርፍ ህዳግን በፋብሪካዎች ዋጋ የተለያየ በመሆኑ ከታኅሣሥ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በፊት በነበረው ዋጋ እንዲሸጥ መወሰኑንም ገልጸዋል፡፡

ቸርቻሪዎች ከአከፋፋዮች ከገዙበት ዋጋ በኩንታል 20 ብር ትርፍ ጨምረው እንዲሸጡ መወሰኑንም አቶ ወንድሙ  አመልክተዋል፡፡

መንግሥት ከወሰነው ዋጋ በላይ በሚሸጡ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡

በምርቱ ላይ በየጊዜው የሚታየውን የስርጭት ችግርና የዋጋ ጭማሪ በዘላቂነት ለመፍታትም የአሠራር መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መመሪያው እንደጸደቀም ወደ ሥራ እንደሚገባም  ኃላፊው  ተናግረዋል፡፡

የሲሚንቶ ዋጋ በቅርቡ በመናሩ መንግሥት ጭማሪ ባደረጉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም