የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሠራተኞች ኮሮናን ለመከላከል የ50 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሠራተኞች ኮሮናን ለመከላከል የ50 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2012 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ኮቪድ -19ን ለመከላከል የ50ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በድጋፍ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጀኔራል አደም መሐመድ ድጋፉን ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክበዋል።
ጄኔራል አደም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሠራዊቱ የአገርን ድንበርና የዜጎችን ሰላም ከማስከበር ባሻገር በማንኛውም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈ ሕዝቡና አገሩን በግንባር ቀደምትነት እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ የሠራዊቱ እዞች በራሳቸው ተነሳሽነት በዛሬው ዕለት 4 ሚሊዮን 785ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ሠራዊቱ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም እስካለፈው ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 1ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መስጠታቸውን ጄኔራል አደም ተናግረዋል።