ከአዲስ አበባ ለዕድገታችን የሚጠቅሙ በርካታ ልምዶች ወስደናል ... ጎንደርና አምቦ ከተሞች - ኢዜአ አማርኛ
ከአዲስ አበባ ለዕድገታችን የሚጠቅሙ በርካታ ልምዶች ወስደናል ... ጎንደርና አምቦ ከተሞች
አዲስ አበባ ግንቦት 27/2012(ኢዜአ) የጎንደርና የአምቦ ከተሞች የሕብረተስብ ተወካዮች ከተሞቻቸውን ለማሳደግ የሚጠቅሟቸውን ልምዶች ከአዲስ አበባ መውሰዳቸውን ተናገሩ።
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው አዲስ አበባ ከተሞቹ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ታግዛለች ብለዋል።
የሁለቱ ከተሞች ከንቲባዎችና የሕብረተሰብ ተወካዮች በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የሸገርን ማስዋብና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል ውይይትም አድርገዋል።
የሕብረተሰብ ተወካዮቹ በቀዳሚነት የጎበኙት11 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነውንና በውስጡ የእምነት ተቋማት፣ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች፣ ፈረስ መጋለቢያና የተለያዩ መዝናኛዎችን ያካተተውን የእንጦጦ ፓርክ ነው።
ግንባታው በአራት ቢሊዮን ብር እየተካሄደ የሚገኘውንና የአድዋን ምንነት የሚያንፀባርቀውን የ"አድዋ ማዕከል"ም ጎብኝተዋል።
ከህጻናት እስከ አዋቂ ከ35 ሺህ በላይ ሰዎች በአንድ ላይ ሊያነቡበት የሚችሉት የአዲስ አበባ ቤተ መፃህፍት ግንባታም በተወካዮቹ ከተጎበኙት ስፍራዎች አንዱ ነው።
'የወንድማማችነት ማዕከል' ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ስም ተጽፎ የተቀመጠበትና በአንድ ጊዜ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች መሰባሰቢያም ተጎብኝቷል።
የከተሞቹ ተወካዮች ባዩት ሁሉ መደነቃቸውንና በአዲስ አበባ እየተሰራ ያለው ስራ ለእነርሱ ከተሞች ትልቅ ልምድ መሆኑን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም እንዳሉት በአዲስ አበባ እየተሰራ ያለው ስራ በርካታ ትምህርት ይሰጣል።
በእንጦጦ ተራራ ያዩት ነገር እንዳስደነቃቸው የገለጹት ኢንጂነር ማስተዋል ጎንደርም በተራራ የተከበበች በመሆኗ በዚህ ረገድ ትልቅ ልምድ ተወስዷል ነው ያሉት።
የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሳህሉ ድሪብሳም ከምንም በላይ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እንዴት በአጭር ጊዜ መከወን እንደሚቻል መታዘባቸውን ነው የገለጹት።
ሁለቱ ከንቲባዎች ከተሞቻቸው ከአዲስ አበባ ጋር ባላቸው የእህትማማችነት ስምምነት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ "ዛሬ ያየችሁት ዓባይን በጭልፋ ነው" በማለት በከተማዋ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።
በመዲናዋ ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ የሸገርን ማስዋብ፣ የሸገር ዳቦ መጋገሪያ እንዲሁም የለገሃርና ጎተራ ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ።
ጉብኝቱ አዲስ አበባ ዋና ከተማ እንደመሆኗ ቀዳሚ ሚና መጫወት ስለሚኖርባት ሁለቱ እህትማማች ከተሞች እየተሰራ ያለውን ተመልክተው ወደ ራሳቸው እንዲወስዱት ታስቦ ነው ብለዋል።
አስተዳደሩ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች በተሻለ ደረጃ እንዲያድጉ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
አምቦና ጎንደር በአዲስ አበባ ተገናኝተው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን ታሪካዊ ክስተት ብለውታል።
የሁለቱ ከተሞች የሕብረተሰብ ወኪሎች ከተሞቹን የሚያስተስራቸው ነገሮች ሲጠቅሱ ከሶስት ዓመት በፊት ወጣቶቻቸው በተናበበ መልኩ ጨቋኝ ሁኔታዎችን በጋራ መቃወማቸውን አስታውሰዋል።
ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሁለቱን ከተሞች የሚያስተሳስሯቸው ጠንካራ ነገሮች ቢሰነዱ ትልቅ ታሪክ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባና ጎንደር ባለፈው ጥር የእህትማማች ከተማነት ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ከአምቦ ጋር ቀደም ብሎ የተፈረመ ስምምነት እንደነበረ ተገልጿል።