118 ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ አረቢያ ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
118 ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ አረቢያ ተመለሱ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 27 /2012 (ኢዜአ) በሳዑዲ አረቢያ ዲዛን ግዛት እስር ቤት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 118 ኢትዮጵያዊያን በዛሬው ዕለት ወደ አገራቸው ተመለሱ።
በተመሳሳይ ባለፈው ማክሰኞ 136 ዜጎች ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን ፤ በአጠቃላይ 254 ኢትዮጵያውያን ተመልሰዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለችግር ተጋልጠዋል።
በሳዑዲ አረቢያ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንም በወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት በችግር ውስጥ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው።
ዜጎቹን ወደ አገራቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግስት ሲሰራ መቆየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠባባቂ ቃል አቀባይ አቶ አምሳሉ ትዕዛዙ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያኑን ወደ አገራቸው ለመመለስ የውጭ ጉዳይ፣ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እና ሰላም ሚኒስቴሮች በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን አቶ አምሳሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ለአገራቸው እንዲበቁ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ወጪውን መሸፈኑን ተናግረዋል።
ዛሬ ወደ አገራቸው ከተመለሱት ዜጎች መካከል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በእስር ቤት ውስጥ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ላይ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
በህገ-ወጥ መንገድ በመሄዳቸው ያላቸው ንብረት እንደተወሰደባቸው ጠቁመው፤ ከእነሱ በተጨማሪ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ዛሬ ወደ አገራቸው በመመለሳቸው በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዜጎቹ ወደ ማህበረሰቡ ከመቀላቀላቸው በፊት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት የሚቆዩ መሆናቸው ተገልጿል።
ከ14 ቀናት ቆይታ በኋላ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደሚደረግላቸውም ተጠቁሟል።