ምክር ቤቱ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚነሱ ውዝግቦች በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚነሱ ውዝግቦች በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አሳሰበ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 27 /2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚነሱ ውዝግቦች በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አሳስቧል፡፡
ምክር ቤቱ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ሠላማዊ ምክክር ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝቧል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ የተከበረው የመጅሊስ ምክር ቤት ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በሚመለከት አገራቱ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት አድርገው መግባባት እንዳለባቸው ያምናል ብለዋል በመግለጫቸው።
አገራቱ ለጋራ ተጠቃሚነት በትብብር መስራት አለባቸው ያሉት ቀዳሚ ሙፍቲ ለወንዙ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያም የበረከቱ ተካፋይ መሆን እንዳለባት ተናግረዋል።
የግብፅ መንግሥትም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በመመስረት ከኢትዮጵያ መንግስት፣ ሕዝብና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር መመካከር ይገባዋል ብለዋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ዑለማዎች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼኸ ቃሲም ታጁዲን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የእውነት ምድር ተብላ የተመሰከረላት፤ ስለ ሕዝቦቿ መልካምነትም የተነገረላት ነች ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያስፈልጋቸው መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።
ዜጎቿም የአገሪቷን ተፈጥሯዊ ሃብት ተጠቅመው የመልማትና የማደግ ሰብዓዊ፣ ሕጋዊ፣ ኃይማኖታዊና ተፈጥሯዊ መብታቸው እንደሆነም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያና የግብፅ ሕዝቦች በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በኃይማኖት፣ በትምህርት፣ በመልክዓ-ምድርና በታሪክ የረጅም ጊዜ ትስስር እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
ሼኸ ቃሲም ግብፅ የዓባይን ውሃ በብቸኝነት ለመጠቀም የያዘችው አቋም እንዳሳዘናቸውም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት በተለይም በልዩነት ከቆመችው ግብፅ ጋር ስለ ግድቡ ሲካሄድ የቆየውን ምክክር ምክር ቤቱ በቅርበት ሲከታተል መቆየቱን ጠቅሰው፤ የነበረው የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ተገቢ እንዳልነበረ ተናግረዋል።
ለግብፅና ለሱዳን መንግስታት፣ ለአል አዝሀር ዩኒቨርሲቲ፣ ለግብፅ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና ለግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ድርድሩ በሠላም እንዲያልቅ ከልባቸው እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዘር፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በሌሎች ምክንያቶች ሳይከፋፈሉ ግድቡን ዳር የማድረስ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በግድቡ ዙሪያ የሚነሱ ውዝግቦች በሠላም እንዲፈቱ ከሱዳንና ከግብፅ ሕዝቦች ጋር ከቦታው ድረስ በመሄድ ምክክር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።