ቀጥታ፡

ለወልድያ ጠቅላላ ሆስፒታል የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ

ወልድያ፣ ግንቦት 27/2012 (ኢዜአ) የወልድያ ጠቅላላ ሆስፒታል በሳዑዲ አረቢያ ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ከ640 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አገኘ ።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሐ የኋላ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት መሳሪያዎቹ በድጋፍ መገኘታቸው የህክምና አገልግሎቱን ጥራትና ፍጥነት ለማሻሻል ያግዛሉ ።

የኮሮና በሽታ መከሰትን ተከትሎ ሆስፒታሉ የሚያስፈልጉትን የህክምና መሳሪያዎች በጥናት በመለየት የአካባቢው ተወላጆች እንዲያሟሉ ጥሪ መደረጉን አስታውሰዋል ።

ጥሪውን ተከትሎ የተደረገው ድጋፍ 44 የልብ ምት መቁጠሪያና መመርመሪያ፣ ከሳምባ ፈሳሽን በመምጠጥ አየር የሚሰጥ ኦክስጂን ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና ሌሎች የህክምና መሳሪያዎች ያካተተ ነው ብለዋል ።

በድጋፍ ከተገኙ መሳሪያዎች ውስጥም የተወሰኑትን ለመርሳና ለቆቦ ሆስፒታሎች በመስጠት ማህበረሰቡ በቅርበት አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል ።

የአካባቢው ተወላጆች የአገር ውስጥ ኮሚቴ አስተባባሪው ዶክተር አብዱልከሪም መሀመድ በበኩላቸው ማሽኖቹ የተገዙት በመካ፣ በመዲናና በጂዳ የሚኖሩ የሰሜን ወሎ ዞን ተወላጆች በለገሱት 640 ሺህ 900 ብር ነው።

በአረብ አገራት የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ከአሁን በፊትም የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን ገዝተው ለሆስፒታሉ ማስረከባቸውን ጠቁመው፤ ተመሳሳይ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የወልድያ ሆስፒታል በአሜሪካ ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ከ406 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኦክስጂን ሲሊንደሮችና የጌጅ ማሽኖችን በእርዳታ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም