ኦቲዝም ላለባቸው ልጆች የሚያገለግል ለይቶ ማቆያ መዘጋጀቱ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ኦቲዝም ላለባቸው ልጆች የሚያገለግል ለይቶ ማቆያ መዘጋጀቱ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 27 /2012 (ኢዜአ) ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ የአዕምሮ እድገት ውስንነት (ኦቲዝም) ላለባቸው ልጆች የሚያገለግል ለይቶ ማቆያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገለፀ።
ኅብረተሰቡ የኦቲዝም ጤና እክል ያለባቸውን ልጆች ከየትኛውም የማህበረሰብ ክፍሎች በተለየ ሁኔታ ድጋፍ ይሻሉና ለወላጆቻቸው የሞራልና የአቅም ድጋፍ እንዲሰጥም ጥሪ ቀርቧል።
ወይዘሮ አበሩ ዳመሳ ልጃቸው ፍቅርተ ወንድወሰን ኦቲዝም ያለባት ስትሆን እስከ አምስት ዓመቷ ድረስ ከአባቷ ጋር በመሆን ኑሮን ሲገፉ ቆይተዋል።
ሆኖም አምስት ዓመት እንዳለፋት የአባቷ ህይወት በማለፉ የእናቷ ኑሮ ከበደ፤ ኑሯቸውን ለመምራትም ብቸኛው መፍትሄ ልጃቸውን በቤት አስረው ያገኙትን ሥራ በመስራት ኑሯቸውን መደጎም ነው።
እናም ሆድ ጠግቦ እንዲያድር ኑሮም እንዲገፋ ልጃቸውን በገመድ እያሰሩ በሰው ቤት በመዞር ልብስ እያጠቡና ሌሎችንም የቤት ውስጥ ሥራዎችን እያከናወኑ ማሳለፍ ጀመሩ።
ለአንድ ዓመት ከግማሽ ያህል የፍቅርተ እጣ-ፈንታ እቤት ውስጥ መዋል፣ የእናቷም የእለት ተግባር በየሰዉ ቤት እየተንከራተቱ ራሳቸውንና ልጃቸውን መመገብ ነበር፤ ሆኖም ግን የዛሬ 15 ዓመት ወደ ጆይ ኦቲዝም ማዕከል ጎራ ብለው ችግራቸውን በማዋየታቸው ለልጃቸው መዋያ ለሳቸውም መፍትሄ ማግኘታቸውን ነግረውናል።
ወይዘሮ አበሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ላለፉት 15 ዓመታት ልጃቸው በማዕከሉ እየተማረች እሳቸውም በማዕከሉ ውስጥ የባልትና ውጤቶችን እያዘጋጁ ሲሰሩ ቆይተዋል።
አሁን ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ከልጃቸው ጭምር ቤት ለመዋል ተገደዋል።
ልጃቸው ፍቅርተ ቤት በመዋሏ ምክንያት ከዚህ ቀደም የማይታይባትን ብስጭት እያሳየች መምጣቷን ነው የገለፁት ወይዘሮ አበሩ።
''የእኛ ልጆች ከሌላው በተለየ ድምፅ የሚሆናቸው ይፈልጋሉ ድጋፍንም እምንጠይቀው የእነሱ ድምፅ ሆነን ነው'' ያሉት ወይዘሮዋ፤ ተመሳሳይ ችግር ያለበት የጓደኛቸው ልጅ ቤት አልቀመጥም በማለቱ በየሰፈሩ አብረው ለመሄድ መገደዳቸውን ይናገራሉ።
ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል በተለየ ሁኔታ እነዚህ ልጆች ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ ለማስቻልም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ዘሚ የኑስ እንዳሉት፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች የተለየ ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል።
''በየቀኑ የሚያደርጉት አኗኗርና ሥራቸው ድግግሞሽ በመሆኑ፣ ሂደቱ በሚቋረጥበት ወቅት ባህሪያቸውና ስሜታቸው ላይ ተፅዕኖ ያመጣባቸዋል፤ አዲሱን ህይወት ለመልመድም ይቸገራሉ'' ነው ያሉት።
ይህም የመረበሽ ስሜት እንደሚፈጥርባቸው ገልጸው፤ ''ወላጆችም በቤት ውስጥ የሚረዳቸው ከሌለ ልጆቹ ከዚህ በፊት እንደነበረው እንዲታሰሩና በር እንዲዘጋባቸው የሚያስገድድ ሁኔታ ይፈጥራል'' ብለዋል።
''ኮሮናቫይረስ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆችና ወላጆች ላይ ሊገኝ ይችላልና በዚህ ወቅት ወላጆች ወደ ለይቶ ማቆያ ቢገቡ ልጆቹ ምርመራ እስኪደረግላቸው ድረስ የሚቆዩበት ቦታ በማዕከሉ ውስጥ ተዘጋጅቷል'' ብለዋል።
የተዘጋጁት 12 አልጋዎች መሆናቸውን ገልፀው፤ ከጤና ሚኒስቴርና ከማዕከሉ የተውጣጡ ስድስት ባለሙያዎች ዝግጁ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት ሥራው እንደሚጀመርም ነው የተናገሩት።
ለይቶ ማቆያዎቹ የተዘጋጁት በጤና ሚኒስቴርና በማዕከሉ ትብብር መሆኑን ገልፀው፤ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ደግሞ ልጆቹ ቫይረሱ ከተገኘባቸው እንዲታከሙ ዝግጅት ተደርጓል።
ይህ ዝግጅት ጅማሬ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ ዘሚ፤ ''ከዚህ ልምድ በመውሰድ ቁጥሩ ቢጨምርና ተጨማሪ ቦታ ቢያስፈልግ ከሌሎች ጋር ይሰራል'' ብለዋል።
አብዛኛዎቹ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች የሚጥል በሽታ (ኢፕሊፕሲ) በተጓዳኝ ያለባቸው በመሆናቸው ማዕከሉ ከአማኑኤል ሆስፒታል ጋር በመተባበር መድኃኒት እንዲያገኙ ለማስቻልም በዝግጅት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ማዕከሉን ከግለሰቦችና ተቋማት የሚመጣለትን ድጋፍ ከማከፋፈል በዘለለ በአካል በመገኘት ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉትንም የማገናኘት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዚህ መንገድ እስካሁን ድረስ ከ50 በላይ ሰዎች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
ቤት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ በድግግሞሽ ልጆቹን በስዕላዊ መግለጫና በመዝሙር በማስተማር ርቀትን ለማስጠበቅና እጅን እንዲታጠቡ ማድረግ እንደሚቻል ያስረዱት ወይዘሮ ዘሚ፤ ልጆቹን ማስተማር የየእለት ተግባር ማድረግ እንደሚገባም ነው ያብራሩት።
ኦቲዝም የአዕምሮ እድገት ውስንነት እክል ሲሆን የልጆች ከሰዉ ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነትና የመግባባት ችሎታ/ክህሎት እንዲሁም አጠቃላይ የመማር እና የአስተሳሰብ ሂደት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡