የዘንድሮውን ሃገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ለማስጀመር ሃዋሳ ተዘጋጅታለች - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮውን ሃገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ለማስጀመር ሃዋሳ ተዘጋጅታለች
ሐዋሳ፣ ግንቦት 27/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ሐዋሳ ከተማ ነገ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ቀን የቅድመ ዝግጅት ስራ መገባደዱን የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማሞ ጎዴቦ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሃገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀንን በይፋ ለማስጀመር ሀዋሳ ሀይቅ ዳር የሚገኘው ታቦር ተራራ ተመርጧል።
ቀደም ሲል የጉድጓድ ቁፋሮ የተከናወነ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ተራራው ላይ የሚተከሉ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ችግኞች መጓጓዛቸውን ጠቁመዋል።
"ከሚተከሉት ሀገር በቀል ችግኞች ውሰጥ አብዛኛው ወይራ፣ዝግባ፣ዋንዛና ጽድ ሲሆኑ ሌሎችም የውጭ ዝርያ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ ተደርገዋል" ብለዋል።
እነዚህ ዝርያዎች ለሐዋሳና አካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚና አፈርን ቆንጥጠው በመያዝ የመሬት መሸርሸርን ለመከላከል ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከሀገር አቀፉ ዘመቻ ባለፈ በክልሉ ዘንድሮ 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ "በነገው የአረንጓዴ አሻራ ቀን ብቻ በክልሉ 25 ሚሊዮን ችግኝ ይተከላል ተብሎ ይጠበቃል "ብለዋል።
በነገው መርሃ-ግብር ላይ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በተራራው ላይ በሚካሄደው ችግኝ ተከላ ቢበዛ 100 የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ርቀታቸውን ጠብቀው እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ልማት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ቢተው ሽባባው በበኩላቸው "እንደ ሀገር 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እያንዳንዱ ክልል የራሱን እቅድ አውጥቶ እየሰራ ነው" ብለዋል።
አሁን ላይ በጉድጓድ ቁፋሮውና በተከላ ሳይት መረጣ እየተደረገ ያለው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።