ተጨማሪ 150 ሰዎች ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው፤ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል - ኢዜአ አማርኛ
ተጨማሪ 150 ሰዎች ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው፤ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል
ግንቦት፤ 27/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 5141 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 150 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1636 መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠ ሰዎች ከ 3 እስከ 72 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ 94 ወንድና 56 ሴት ሲሆኑ፤ 147 ኢትዮጵያውያንና ሶስቱ የውጭ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 123 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 1 ሰው ከአፋር፣ 2 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 3 ሰዎች ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ 2 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 13 ሰዎች ከአማራ ክልል እና 6 ሰዎች ከሶማሌ ክልል መሆናቸው ተገልጿል።
ኮሮና ቫይረስ በምርመራ ተገኝቶበት በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት የነበረ፤ ከዚህ ቀደም ተጓዳኝ ህመም ያለበትና በጽኑ ህክምና ላይ የነበረ የ30 ዓመት ኢትዮጵያዊ ትላንት ህይወቱ በማለፉ እስካሁን በቫይረሱ የ 18 ሰዎች ህይወት አልፏል።
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወቱ የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቹ መጽናናትን ተመኝተዋል።
በሌላ በኩል ትላንት 4 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች 250 ሆኗል።
በአጠቃላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ 1366 ሰዎች ሲሆኑ ከነዚህ መካከል 16ቱ በፀና የታመሙ መሆናቸውን ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።
የላቦራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወኑ መሆኑም ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትሯ እንደገለጹት የላቦራቶሪ ውጤቶች የሚያሳዩት በህብረተሰቡ ውስጥ ባለው የቫይረሱ ስርጭት ምክንያት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከእለት እለት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል።
ለዚህም እንደ ማሳያ የመጀመሪያው ሰው ቫይረሱ እንዳለበት ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ባለፉት ሁለት ሳምንታት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ 300 ፐርሰንት በላይ ጭማሪ ማሳየቱም ተጠቅሷል።
እስካሁን አጠቃላይ 125, 570 የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።