በቀጣዩ ሣምንት ለሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት የሚሆን 1 ሺህ ሄክታር መሬት ምንጣሮ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣዩ ሣምንት ለሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት የሚሆን 1 ሺህ ሄክታር መሬት ምንጣሮ ይጀመራል
አዲስ አበባ ግንቦት 27/2012 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት የሚሆን አንድ ሺ ሄክታር የመሬት ምንጣሮ ስራ በመጪው ሣምንት እንደሚጀመር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ።
ለምንጣሮ ስራው 300 ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት መደራጀታቸውም ታውቋል።
ኢዜአ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰንና የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ን በስልክ አነጋግሯል።
አቶ አሻድሊ እንደገለጹት ቀደም ሲል በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ተጀምሮ የነበረው የደን ምንጣሮ ውጤታማ አልነበረም።
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ስለ መሆኑ ገልጸው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት መሆኑን ገልጸው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግንባታ ቦታው የሚገኝበት በመሆኑ ኃላፊነቱ 'እጥፍ ይሆናል' ብለዋል።
ግድቡን በመጪው ሐምሌ ውሃ ለመሙላት በታቀደው መሰረት ክልሉ ለዚህ የሚሆነውን መሬት የደን ምንጣሮ ለማካሄድ መዘጋጀቱን አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ በጥቃቅንና አነስተኛ ከተደራጁ ወጣቶች በተጨማሪ በቀን ስራ የሚተዳደሩ ዜጎችም በምንጣሮ ስራው ይሳተፋሉ።
አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ለመመንጠርና ለተያያዥ ስራዎች ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል ብለዋል።
ወጪው ግንባታውን በሚያከናውነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚሸፈንም ገልጸዋል።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀከት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው የግድቡን ግንባታ በዕቅዱ መሰረት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ውሃ ለመያዝ በተዘጋጀው ግድብ ውስጥ የሚተከሉ የብረታብረት ስራዎች ተጠናቀው ኮንክሪት እየተሞላባቸውና የውሃ መግቢያ መቆጣጠሪያ በሮችም እየተገጠሙ መሆኑን ገልጸዋል።
አብዛኛው ስራ መጠናቀቁን የገለጹት ኢንጂነሩ ቀሪ ስራዎችም በተያዘላቸው ጊዜ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።
በሌላ በኩል የፕሮጀክቱ የግንባታ ሠራተኞች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ጠብቀው ስራቸውን እንዲያከናውኑ እየተወሰዱ ስለሚገኙ እርምጃዎች ኢንጅነር ክፍሌ አስረድተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 73 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል።
በመጪው ሐምሌ በግድቡ የሚሞላው የውሃ መጠን 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ሲሆን ይህም የግድቡን ሁለት ተርባይኖች የሚያንቀሳቅስ ነው።
በሚቀጥለው ዓመት በተመሳሳይ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሊትር ውሃ ይሞላል ተብሏል።