የድንበር አካባቢ እንቅስቃሴ በመገታቱ ለችግር ተጋልጠናል--ነዋሪዎች

አሶሳ ግንቦት 26 / 2012 (ኢዜአ) በቤኒንሻጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ድንበር አካባቢ የሚታየውን ህገ-ወጥ የሰዎች እንቅስቃሴ እየተገታ በመምጣቱ የመተዳደሪያ ገቢያቸው በመቋርጡ ለችግር መጋለጣቸውን አንዳንድ የኩርሙክ ነዋሪዎች ጠየቁ ፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ጣእመ ገብረስላሴ የተባሉ የኩርሙክ ነዋሪ እንደገለፁት ቫይሱን ለመከላከል ሲባል የድንበር አካባቢ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መዘጋቱ ጥሩ ቢሆንም እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ወገኖች ስራ እንዳሳጣቸው አስረድተዋል፡፡

አብዛኞቹ የኩርሙክ ከተማ ነዋረዎች ኑሮአቸውን በድንበር የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው በአሁኑ ወቅት ለእለት ጉርሳቸው የሚቸገሩ ሰዎች እንዳሉ ተናግረዋል ።

የስድስት ዓመት ልጃቸውን በስኳር ችርቻሮ እንደሚያሳድጉ የሚናገሩት ወይዘሮ ቦሰና ብዙነህ በበኩላቸው በቅርቡ በድጋፍ ያገኙት 10 ኪሎ ዱቄትና ዘይት በማለቁ መቸገራቸውን ተናግረዋል ።

ቫይረሱን ለመከላከል ከቤት ውስጥ መቀመጥ ቢመከርም የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን በድንበር አካባቢ ለሽያጭ የሚውል እንጨት ለማሰባሰብ እንደሚወጡ ነዋሪዋ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ድንበር አቋርጠው ከሚገቡ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንደሚገናኙ አስተያየት ሰጪዋ ጠቁመዋል፡፡

ኮሮናን ፈርቼ ልጄ በረሃብ ስትሞት ማየት አልፈልግም የሚሉት ነዋሪዋ አስቸጋሪ ሥራዎችን ሁሉ በማከናወን የራሴን እና የቤተሰቤን ህይወት ለማስቀጠል እየጣርኩኝ እገኛለሁ ብለዋል፡፡

በድንበር አካባቢ ህገ ወጥ የሰዎች እንቅስቃሴ ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በሓሳብ ደረጃ የምንደግፈው ቢሆንም በተግባር ግን የሚላስ የሚቀመስ እያሳጣን በመሆኑ መንግስት ፣ ባለሃብቱና ህብረተሰቡ ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባል ብለዋል ።

የምንበላው ካገኘን እኛም ከሚመለከታቸው የፀጥታ ኃይሎች ጎን በመቆም የበኩላችንን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል ።

የኩርሙክ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እስማኤል አብዱራህማን እንዳሉት በወረዳው በእርሳቸው የሚመራ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረሃይል ተቋቋሞ በተለይም በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የሚገቡትን ለመከላከል እየሠራ ነው ።

ቫይረሱ ያስከተለውን ተጽእኖ ለመቋቋም መተዳደሪያቸውን በድንበር ንግድ ብቻ ያደረጉና ለከፋ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት በቅርቡ የምግብ እና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም ብለዋል ።

ግብረሃይሉ ህብረተሰቡን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ ለማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉን አቶ እስማኤል ገልፀዋል ።

የክልሉ መንግስትም አስፈላጊው  እገዛ እንዲያደርግላቸው  ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ ኮሮና ቫይረስ መከላከል አብይ ግብረ ኃይል አባልና የጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በበኩላቸው በክልሉ ኩርሙክ ድንበር በኩል ህገ-ወጥ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለማቆም በተደረገ ጥረት ውጤት መገኘቱን ይናገራሉ፡፡

የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ችግሩን ለመፍታት በገንዘብ፣ በቁሳቁስ ፣ በተሽከርካሪና መሰል ግብዓቶች ለመደገፍ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም