የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመቀነስ የምሁራን ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመቀነስ የምሁራን ተሳትፎ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 26/2012 በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ምሁራን የሚያቀርቡት ምክረ ሃሳብ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ኮቪድ 19 በግብርና እና በምግብ ዋስትና ላይ የሚያደረሰው ተፅእኖ እና መፍትሔዎቹ በሚል ሃሳብ ከተለያዩ ምሁራን ጋር በዌቢናር (የቪዲዮ) ውይይት አድርጓል።
ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ኮቪድ 19ን ለመከላከል ምሁራን የሚያቀርቡት ምክረ ሃሳብ ወሳኝ ነው።
በዛሬው እለት በዘርፉ ምሁራን የሚደረገው ውይይትም ግብርናው ዘርፉ ለሚገጥሙ ችግሮች መፍትሔ የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል።
በምሁራኑ የሚቀርቡት መፍትሄዎችና ምክረ ሐሳቦችም ለሚመለከተው አካል ቀርበው ዘረፉን ለማዘመን አጋዥ ይሆናሉ ብለዋል።
የግብርና ሚኒሰትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው የግብርናውን ሴክተር ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት ቢከወኑም አሁንም ውስብስብ ችግሮች አሉበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛቷ በአፍሪካ በሁለተኛነትመቀመጧን ጠቅሰው ለህዝቡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘርፉን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ በግብርናው ዘርፍ ከሰለጠኑ ምሁራን ጋር በመስራት ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ፍቃዱ ምትኩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኮሮና ወረርሽ ተጽእኖ ከሚያሳርፍበት መካከል የግብርና ኤክስቴንሽንና የግብአት አቅርቦት ተጠቃሽ ይሆናል።
የአንበጣ መስፋፋትና የጎርፍ መከሰትም በአሁኑ ወቅት እንደ ችግር የሚታዩና በዘርፉ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የሕብረት ስራ ማሕበራትን ማሳተፍ፣ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመለወጥ ጥረት ማድረግና ገበያዎችን ማስፋፋት ችግሩን ለማቃለል ከሚቀመጡ መፍትሔዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆኑን አብራርተዋል።
ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዶክተር አለማየሁ ስዩም እንዳሉትም ኮቪድ 19 በግብርና የምግብ ዋስትና ስርአት ላይ ተጽእኖው ከባድ ነው።
የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የቤት ውስጥ የመቀመጥ፣ ትምህርት ቤቶች መዘጋትና እንቅስቃሴዎችን መገደብ እራሱን የቻለ ተጽእኖ የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል።
ችግሮቹን በዘላቂነት ለማስወገድም ማህበረሰቡ ቫይረሱን እንዲከላከል ማስቻል ቁልፍ ተግባር መሆኑ ተመልክቷል።
የቪዲዮ ውይይቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።