ቀጥታ፡

ለአምስት ከተሞች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ደብረ ብርሃን፣ መተማ፣ ደሴ፣ ሐዋሳ፣ አምቦ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) በተለያዩ አምስት ከተሞች በኮሮና ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብና የቁሰቁስ ድጋፍ ተደረገ።

በአማራ ክልል በደብረብርሃን፣ በደሴና በመተማ ከተሞች የተለያዩ ተቋማትና ባለሀብቶች በኮሮና ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፉን ያደረጉት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ በመተማ የሚገኘው የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅትና ሁለት የአዲስ አበባ ነዋሪ ባለሀብቶች ናቸው።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉሥ  ታደሰ እንደገለጹት በኮሮና ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖችና ለተለያዩ ተቋማት የተሰጠው ድጋፍ በ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የተገዛ 500 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ ጤፍና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ነው።

በተያያዘ ዜና የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት የመተማ አካባቢ አስተባባሪ አቶ ዓልአዛር ሞላ እንዳሉት በምዕራብ ጎንደር ዞን ለሚገኙ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት አገልግሎት የሚውል 400 ሺህ ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

ከተደረጉት የቁሳቁስ ድጋፎች መካከልም 500 ብርድ ልብስ፣ ሁለት ድንኳኖች፣ ሁለት ሺህ ሣሙና፣ የምግብ ማብሰያ ዕቃዎች፣ ሳኒታይዘርና ሌሎች ቁሳቁሶች ይገኝበታል።

በሌላ በኩል ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑት ኡስታዝ አቡበከር አህመድና አቶ አብዱ ይመር በበኩላቸው አንድ ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የምግብ እህልና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

በደሴ ኮምቦልቻ ለሚኖሩ ከሁለት ሺህ በላይ አቅመ ደካሞች ለእያንዳንዳቸው 20 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ ሩዝና ሦስት ሊትር ዘይት በዛሬው ዕለት መከፋፈሉን ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ተናግረዋል።

አቶ አብዱ ይመር የተባሉ ባለሀብትም 50 የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎች፣ 50 የሙቀት መለኪያ መሣሪያ፣ 50 ለጤና ባለሙያዎች የሚሆኑ ሙሉ አልባሳት ለግሰዋል።

በደብረብርሃን፣ በደሴና በመተማ ዕርዳታውን የተረከቡ የግብረኃይል አባላት ምሥጋናቸውን አቅርበው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ለሲዳማ ዞን አስተዳደር አስረክባለች።

በቤተክርስተያኗ የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን የማዕከላዊ ደቡብ ኢትዮጰያ ሲኖዶስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዝናሽ ፀጋዬ እንደገለጹት ድጋፉ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እንዲያግዝ ታስቦ የተደረገ ነው።

ከተደረገው ድጋፍ መካከል ለጤና ባለሙያዎች የሚሆን ከሁለት ሺህ በላይ የአፍንጫና አፍ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ 31 አልባሳት፣ ከአንድ ሺህ በላይ የእጅ ጓንት፣ የውኃ ማጠራቀሚያና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።


በተጨማሪም ከ700 ሊትር በላይ የንጽሕና መጠበቂያ ሳኒታይዘር፣ 1 ሺህ 300 ካርቶን ሣሙና፣ 40 ሊትር አልኮልና ሌሎች የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሚረዱ ቁሳቁሶች አነስተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች እንዲከፋፈል በስጦታው ተካቷል።

የሲዳማ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊና የግብረ ኃይሉ አባል አቶ በላይነህ በቀለ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት ቤተክርስቲያኗ የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ላደረገችው ድጋፍ አመስግነዋል።

በተመሣሣይ ሁኔታ የአምቦ ከተማ አስተዳደር በኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ለተቸገሩ 54 የአካል ጉዳተኞች ድጋፍ አድርጓል።

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ታምራት ሙለታ እንደገለጹት ድጋፉ የተገኘው ከበጎ አድራጊዎች  ነው።

ለአካል ጉዳተኞቹ በነፍስ ወከፍ 25 ኪሎ ግራም ዱቄት እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ታምራት ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው የአካል ጉዳተኞች እገዛው ጊዚያዊ ችግራቸው እንደሚያቃልላቸው በመግለጽ ለወደፊቱም ቢሆን ተመሣሣይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

በዊልቸር እየታገዙ ከሁለት ዓመት ልጃቸው ጋር በጎዳና የሚኖሩት የአምቦ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እቴነሽ ሰርቤሳ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ለወደፊቱም ኅብረተሰቡ እንዲያግ፣ቸው ተማጽነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም