ቀጥታ፡

በአርባምንጭ ከተማ በቤት ለቤት ልየታ ከ130 ሺህ በላይ ሰዎችን ተደራሽ አደረገ

አርባ ምንጭ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) በአርባንጭ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በተካሄደው የቤት ለቤት ልየታ ስራ ከ130 ሺህ በላይ ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን የከተማው አስተዳደር ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የግብረ ኃይሉ አባልና የአስተዳደሩ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማላ ሾኔ  ለኢዜአ እንደተናገሩት  የቤት ለቤት አሰሳው የተካሄደው በአራቱ የአርባምንጭ ክፍለ ከተሞች ነው።

ካለፈው ከሚያዚያ ወር ጀምሮ እስካሁን  በተካሄደው አሰሳ የ52 ሺህ አባወራ ቤቶች የሚኖሩ  ከ130 ሺህ በላይ ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።

ቤት ለቤት በተደረገው ልየታ ስራ  የቫይረሱ  ምልክት የታየበት ሰው እንዳልተገኘ ኃላፊው አስታውቀዋል።

ይህም ሰራ አሁንም ቀጥሎ እንዳለ ያመለከቱት ኃላፊው አሰሳው ቫይረሱ በማህበረሰቡ ውስጥ እንዳይስፋፋ አስቀድሞ ለመከላከል ፋይዳው የጎላ በመሆኑ  ህብረተሰቡ ለጤና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአርባ ምንጭ የሲቀላ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ስንሻው አበበ በበኩላቸው የቤት ለቤት አሰሳው መጀመሩ በሌሎች በሽታዎች ህመም ላይ ያሉትን ጭምር  ለማግኘትም ማገዙን ገልጸዋል።

"የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች ያሉባቸው ሰዎች  ለመለየት የሙቀት መለኪያ መሣሪያ ከመጠቀም በላይ በቃለ መጠይቅ የእያንዳንዱን ቤተሰብ መረጃ በጥንቃቄ እያጠናቀርን ነው" ያሉት ደግሞ በነጭ ሳር ክፍለ ከተማ የእድገት በር ቀበሌ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ  ሲስተር አስራት አለማየሁ ናቸው።

ህብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርገው  ጥንቃቄ ክፍተት እንዳለበት ያመለከቱት ሲስተር አስራት እንደ ዕድል ሆኖ ምልክቱ የታየበት ሰው  እንዳላጋጠማቸው ገልጸዋል።

በነጭሳር ክፍለ ከተማ የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሳራ ተፈራ በሰጡት አስተያየት እራሳቸውን ከበሽታው ለመጠበቅ  የአፈን አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ከመጠቀም ጀምሮ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች ቡድን ቤት ለቤት አሰሳ ማድረጉ ለደህንነታችን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል "በተለይ ምልክቱ የታየበት ሰው ህብረተሰቡ ውስጥ ሊደበቅ ስለሚችል ምርመራው ግለሰቡንም ሆነ ማህበረሰቡን ህይወት ለመታደግ ይረዳል "ብለዋል።

በአርባምንጭ ከተማ ከ300ሺህ በላይ  ህዝብ እንደሚኖር የሚገመት መሆኑን ሪፖርተራችን ከአርባምንጭ ዘገቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም