ቀጥታ፡

በሰሜን ሸዋና ምዕራብ ጎንደር ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዝ የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ደብረ ብርሃን፣ መተማ ግንቦት 26/20212 (ኢዜአ) በሰሜን ሸዋና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያግዝ የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ካደረጉት መካከል በአዲስ አበባ የአማራ ወጣቶች ማኅበር አባል ወጣት ዘነበ በለጠ እንደገለጸው ማኅበሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እያገዘ ይገኛል።

በዚህም 200 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ከእጅ ንኪኪ ነፃ የሆኑ የእጅ መታጠቢያ ዕቃዎች፣ አምስት ሺህ ሊትር የሚይዝ የውኃ ታንከር፣ ፈሳሽ ሣሙና፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ለደብረ ብርሃን ከተማ ሕዝብ ተበርክቷል ብሏል።

ከዚህ በፊትም ማኅበሩ በአምቦ ከተማ ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሶ በቀጣይም በሽታው እስኪጠፋ ድረስ አባላቱን በማስተባበር ተመሳሳይ ድጋፍ በሌሎች አካባቢዎች እንደሚያደርግ አመልከቷል።

የ"ሄልዝ ፎር ፐርሰንስ ዊዝ ዲስኤብሊቲስ" ድርጅት ሰሜን ሸዋ ዞን አስተባባሪ አቶ አበበ ትዕዛዙ በበኩላቸው "ድርጅታቸው በከተማ ለሚገኙ 310 የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሦስት ወር ቀለብ ድጋፍ አድርጓል" ብለዋል።

ከ800ሺህ በር በላይ በመመደብ በነፍስ ወከፍ 15 ኪሎግራም የዳቦ ዱቄት፣ 15 ኪሎ ግራም ፓስታና ማኮሮኒ፣ 10 ኪሎግራም ፈሳሽ ደረቅ ሣሙናና ሌሎች ቁሳቁሶች አበርክተዋል።

በተጨማሪም በወረርሽኙ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ 79 አካል ጉዳት ያለባቸው ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የመኖሪያ ቤት ኪራይ መክፈል መጀመሩንም ጠቅሰዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ  ቫይረሱን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና የፌዴራልና የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መሥሪያ ቤቶች በምዕራብ ጎንደር ዞን ለሚገኙ የለይቶ ማቆያዎች 800 ፍራሽ ድጋፍ ማድረጋቸው ተመልክቷል።

በዞኑ የማኅበራዊ ልማት መምሪያ የጤና ጉዳዮች ክትትል ዋና የሥራ ሂደት ተወካይ አስተባባሪና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ አየነው ማንደፍሮ ድጋፉ በለይቶ ማቆያ የነበረውን ችግር ለማቃለል ያግዛል ብለዋል።

ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ  አመስግነው የጀመሩትን እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የለይቶ ማቆያዎች ከ800 በላይ ከሱዳን ተመላሽ ዜጎች እንደሚገኙ መምሪያው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም