ቀጥታ፡

የሦስት ተቋማት ሠራተኞች ደም ለገሱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) የፌዴራል መንግሥት ሦስት ተቋማት አመራርና ሠራተኞች ደም ለገሱ። ልገሳውን ያደረጉት የፕላን ኮሚሽን፣ የመንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲና የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ናቸው።

አመራሮቹና ሠራተኞች ልገሳውን ያደረጉት በአገር ደረጃ ደም ለመለገስ በቀረበው ጥሪ መሠረት ነው።

በልገሳው ከ70 በላይ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ተሳትፈዋል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ልገሳው የተደረገው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የደም እጥረት ለማቃለል ነው ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ ደም በመለገስ ችግር ውስጥ የሚሰቃዩ ወገኖችን መርዳት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ከወሊድ ጋር በተያያዘና በአደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን እንዲታደግ ኮሚሽነሯ ጠይቀዋል።

በደም እጥረት የሚቸገሩ ወገኖችን በመርዳታቸው ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የተቋማቱ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ናቸው።

ደም ለጋሾቹ  ወደፊትም ደም ለመለገስ ቃል ገብተዋል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት አገራዊ የደም አቅርቦት በመቀነሱ አገራዊ ጥሪ ማከናወናቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም