የትግራይ ህዝብ በህወሃት አገዛዝ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ እንዳያንጸባርቅ ተደርጓል ... የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ

112

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2012(ኢዜአ) ''በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) አገዛዝ የተነሳ የትግራይ ህዝብ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ እንዳያንጸባርቅ ተደርጓል'' ሲል የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ።

የህወሃት ቡድን በትግራይ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው እንደሆነም ፓርቲው ገልጿል። 

የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነቢዩ ስሁል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የህወሃት አገዛዝ በዘር ፖለቲካ ውስጥ "የተነከረ" ህዝብን በመከፋፈልና ሰዎችን በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ነው።

የትግራይ ህዝብ በህወሃት ምክንያት አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ እንዳያንጸባርቅ ጫና እየተደረገበት እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ነብዩ፤ ''ህዝቡ አማራጭ ሃሳብ ሊቀርብለት ይገባል'' ሲሉም ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ይህ እውን እንዲሆን፣ ህዝቡ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ እንዲኖረውና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን  እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

''ህወሃት ህዝብን በመከፋፈል ሰዎችን በማጥቃትና ተገዳዳሪ ሃሳብን በመጨፍለቅ የራሱን ስልጣን ለማራዘም የሚንቀሳቀስ ነው'' ብለዋል።

"ህወሃት ህዝብን እስከ መንደር ድረስ በመከፋፈል ጸረ-አንድነት አቋም ያለው ጠባብ ሃይል ነው" ያሉትአቶ ነቢዩ፤ "ህዝብን በመከፋፈል ለአገዛዙ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የቡድናዊ ጥቅሙን ለማርካት ይንቀሳቀሳል'' ብለዋል።

"የህወሃት አገዛዝ በሂደት ተለውጦ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል" የሚል እምነት በህዝቡ ውስጥ እንደነበረ ያወሱት አቶ ነብዩ፤ በአሁኑ ወቅት በአገዛዙ ላይ ተስፋ የቆረጠው ህዝብ እምቢተኝነቱን እየገለጸ ነው ብለዋል።

በአፈና የሚያምነው የህወሃት ቡድን በትግራይ እየተቀጣጠለ ያለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ለማፈን እየሰራ መሆኑንም አመልክተው፤ ይህም ቢሆን ግን ህዝቡ ማሸነፉ አይቀሬ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሰሞኑ ያወጣው መግለጫ ከህዝብ ጥቅም ጋር የሚጋጭና ስልጣንን ለማራዘም የተደረገ መፍጨርጨር እንደሆነ የገለጹት አቶ ነቢዩ፤ ''መግለጫው የቡድኑ ተስፋ መቁረጥ ማሳያ ነው'' ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲን በአምባገነንነት መክሰስ ከሞራልም ሆነ ከሌሎች መርሆች አንጻር ሲታይ ቡድኑ የከፋ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ መግባቱን የሚያሳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

''ህወሃት ስለአምባገነንነት አንስቶ ሌላውን ለመንቀፍ አንዳችም የሞራል ልዕልና የለውም'' ያሉት የፓርቲው ጽህፈት ቤት ሃላፊ፤ ''ትልቁ የአምባገነን ስርዓት የህወሃት ስርአት ነው'' ብለዋል።

የህወሃት አገዛዝ በኢትዮጵያ ያለውን የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታ የሚያደናቅፍ ቡድን እንደሆነ የተናገሩት አቶ ነቢዩ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ኃይል ለመዋጋት የሚደረገውን ትግል እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ትናንት ባወጣው መግለጫ "የህወሃት አኩራፊዎች የግል ፍላጎታቸውን ለማስቀጠል ያልተቋረጠ ሴራ እየጎነጎኑ ነው" በማለት ማመልከቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም