ቀጥታ፡

በጤና ተቋማት የሚሰሩ 65 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ሚኒስትሯ አስታወቁ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሂደት 49 የጤና ባለሙያዎችና 16 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የስርጭት አድማሱ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

በግንቦት ወር ብቻ ከ1ሺህ ሰዎች በላይ በቫይረሱ መያዛቸውንም ለአብነት አንስተዋል።

የቫይረሱ ስርጭት ከማህበረሰቡ ባሻገር በጤና ተቋማት በሚሰሩ ሐኪሞችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ላይ መከሰቱንም ነው የተናገሩት።

እስካሁን ባለው ሂደትም 49 የሕክምና ባለሙያዎችና 16 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ክትትል እያደረጉ ነው ብለዋል።

ባለሙያዎቹ በአብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የጤና ተቋማት እየሰሩ መሆናቸውን በመግለጽ።

የጤና ባለሙያዎችና የጤና ተቋማት ሠራተኞች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እያደረጉት ላለው ተጋድሎም ምስጋና አቅርበዋል።

መንግሥት የጤና ተቋማት ሠራተኞችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከሚያደርገው ሥራ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ራሱን በመጠበቅ የባለሙያዎቹን ጫና እንዲቀንስም ጠይቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ ማህበረሰቡ የቫይረሱን ስርጭት የሚመጥን ጥንቃቄ አለመደረጉ እንደሚያሳስባቸው ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

"ጥንቃቄ የምናደርገው የጸጥታ አካላት ወይም የጤና ባለሙያዎችን ትዕዛዝ ለማክበር ሳይሆን፤ ለራሳችንና ለምንወዳቸው ወገኖቻችን ብለን መሆን አለበት" ሲሉም ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም