ወረርሽኑን ለመከላከል የወጣቶች ተሳትፎ ቀጣይነት እንዲኖረው ተጠየቀ

59

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የኮቪድ -19 መስፋፋትን ለመከላከል የወጣቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።

በመዲናዋ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ ይታያል ደጀኔ እንደገለጹት በአዲስ አበባ የኮሮናቫይረስ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር በየእለቱ እየጨመረ በመምጣቱ የመከላከል ስራው ተጠናከሮ መቀጠል አለበት።

ለዚህም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ሀብት በማሰባሰብና አካላዊ ርቀት በማስጠበቅ በበጎ ፈቃደኝነት ስራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች ምስጋና አቅርበዋል።

ማህበረሰቡም በሁኔታው ከመደናገጥ ይልቅ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አገሩን ከዚህ ወረርሽኝ ለመጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የክፍለ ከተማው በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅረስላሴ ይርዳው የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመከላከል ከ1 ሺህ 500 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሰልጥነው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከመስጠት በተጨማሪ በሀብት ማሰባሰብ ረገድ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጎ ፈቃደኞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው እንዳሉትም “የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ወጣቶች እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አድንቀዋል።

የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጉልህ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ በሽታው በመስፋፋት ላይ በመሆኑ ጉዳቱን ለመቀነስና ለመከላከል በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም