ቀጥታ፡

ቻይናዊያን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2012 (ኢዜአ) የቻይና ሕዝብ፣ ኩባንያዎችና ሌሎች ተቋማት 520 ሺህ የሚጠጋ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልና ሌሎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡ 

በዛሬው የ10ኛ ዙር የድጋፍ ፕሮግራም ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፉን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂን ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አስረክበዋል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ ድጋፉን ሲረከቡ በመዲናዋ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የቻይና መንግስት፣ ሕዝብና ተቋማት በዚህ በአስቸጋሪ ወቅት ላደረጉት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እያደረገች ባለው ጥረት በቀጣይም የቻይና መንግሥትና ሕዝብን ድጋፍ እንደምትሻም ገልጸዋል።

በቫይረሱ የሚያዙና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ የከተማዋ ነዋሪዎችን ለመርዳት አስተዳደሩ ከኅብረተሠቡ፣ ከባለሃብቶችና ከበጎ ፈቃደኞች ጋር በጋራ እየሰራ ነው።

በአገሪቷ በ25 ሺህ ብሎኮች የምግብ ባንኮችን በማዘጋጀት ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል ኢንጂነር ታከለ።

መዲናዋ ነዋሪ በሽታውን ለመከላከልና የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም ጠይቀዋል።

በድጋፉ የተገኙት ማስኮች ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለጤና ባለሙያዎችና ለፖሊስ አባላት ይከፋፈላሉም ብለዋል።

አምባሳደር ታን ጂን በበኩላቸው ኢትዮጵያና ቻይና ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነታቸው በተጨማሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በቅርበት እየሰሩ ነው ብለዋል።

ቻይና በቫይረሱ ሳቢያ ችግር ላይ በነበረችበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እንዳልተለያት አስታውሰዋል።

የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት እያገዘ ሲሆን፣ ደጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መዲናና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በኮሮና ቫይረስ የሚደርስባትን ተጽዕኖ ለመቀነስ የምታደርገውን ጥረት የቻይና መንግስት ይደግፋልም ነው ያሉት።

ከስድስት የቻይና ተቋማት ከተገኘው ድጋፍ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች፣ የንጽህና መጠበቂያና የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ይገኙበታል።

በተመሳሳይ በ10ኛው ዙር የድጋፍ ፕሮግራም ዛሬ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፉን የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች ማኅበር 1 ሚሊዮን ብር፣ ብርቅዬዎች የፌስ ቡክ ግሩፕ 180 ሺህ ብር የሚያወጣ ቁሳቁስ፣ ካይካድ ኢንጂነሪንግና ሌሎችም አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም