ቀጥታ፡

በኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር የጋላፊ ኬላ ትኩረት ትሻለች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) በኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር ላይ የምትገኘው ጋላፊ ኬላ ኮቪድ-19ን በኮሮና መከላከል ልዩ ትኩረት እንደምትሻ የኬላዋ ሠራተኞች አሳስበዋል።

የአፋር ክልሏ ጋላፊ ኬላ የአገሪቷን 95 በመቶ የወጭና ገቢ ንግድ የምታስተናግድ፤ ከፍተኛ ሙቀት ያላት ትንሽ ከተማ ናት።

ጀማል ሳኒ በኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር የጋላፊ የኮሮናቫይረስ ስክሪኒንግና ለይቶ ማቆያ አስተባባሪ ሲሆን ቦታው ከፍተኛ ፍሰት ያለበት እንደሆነ ይገልጻል።

በቅርቡ ሁለት ባለሙያዎች ቢጨመሩም ላለፉት አራት ወራት ስድስት የጤና ባለሙያዎች ለ24 ሠዓታት የሙቀት ልኬትና ተጓዳኝ ተግባራትን ሲያከናወኑ መቆየታቸውን ነው የተናገረው።

እንደ ሳኒ ገለጻ ከአሽከርካሪዎች በቀር በኬላው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች በሙሉ በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ይገደዳሉ።

እስካሁንም ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች መመርመራቸውንና ከእነዚሁ መካከልም ከ300 በላይ ተጠርጣሪዎች ለይቶ ማቆያ ገብተው 20ዎቹ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ብሏል።

ኢዜአ በጋላፊ ኬላ ተገኝቶ ያነጋገራቸው በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የጣቢያው አስተባባሪ ወጣት ግዑሽ ገምሹ እና የጉምሩክ ከፍተኛ ኦፊሰር ቢንያም ክፍሌ የስፍራውን ሙቀትና የስራቸውን ክብደት ይናገራሉ።

ወጣት ግዑሽ እንደተናገረው ከጅቡቲ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች የኬሚካል ርጭትና ፍተሻ በማድረግ ለ24 ሠዓታት ይሰራሉ።

የአየሩ ሁኔታ ለስራ አመቺ ያለመሆኑና ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ግብዐዓቶች እጥረት መኖሩም ስራውን የበለጠ አስቸጋሪ ማድረጉን ተናግሯል።

አቶ ቢንያም ክፍሌ እንደገለጸው በኬላው የአገሪቱ አብዛኛው ገቢና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴ የሚስተናገድበት ሲሆን በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ሳቢያ የሰራተኞች ቁጥር እንዲቀንስ መደረጉ ስራ ላይ የሚገኙ ሰራተኞች ላይ ጫና ፈጥሯል።

በኬላው የሚገቡ አሽከርካሪዎች ወደ አገሪቱ ከገቡ በኋላ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ ወረርሽኙን የመቆጣጠር ስራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያስከትል በመሆኑም ኬላው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

የጤና ባለሙያው ጀማል ሳኒ ጅቡቲ አካባቢውን በወረርሽኙ ስርጭት ስጋት ቀጣና ውስጥ እንዳስገባችው ገልጾ ለኢትዮጵያም አንዱ የመዛመቻ መስመር ነው ይላል።

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ሁሉንም የአገሪቷን ጫፍ የሚያዳርሱ በመሆናቸው በፈረቃም ቢሆን ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ቢደረግ፤ አልያም በ15 ደቂቃ ውጤት የሚያሳውቅ መመርመሪያ መጠቀም ይገባል ሲል መክሯል።

የጣቢያው ሠራተኞችም በጀማል ሳኒ ሃሳብ ይስማማሉ፤ በተጨማሪም የግል መከላከያ ግብዓቶችና የሰው ኃይል እጥረት ክፍተቶች በሚመለከታቸው ተቋማት እንዲሟሉም ይጠይቃሉ።

በኬላው እያጋጠሙ ያሉ በርካታ ችግሮች  ሰራተኞችን ለወረርሽኙ የማጋለጥ እድሉ ሰፊ በመሆኑ በባለ ድርሻ አካላት ችግሮቹ በፍጥነት ሊፈቱ እንደሚገባም አመልክተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም