ኮቪድ-19 ያስከተለው ሥጋትና የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ቅሬታ - ኢዜአ አማርኛ
ኮቪድ-19 ያስከተለው ሥጋትና የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ቅሬታ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2012 (ኢዜአ) ኮቪድ-19 ያስከተለው ሥጋት አስመልክቶ የድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪዎች ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የከባድ መኪና አሽከርካሪ የሆኑት አቶ ሙሉቀን አዱኛ፣ አቶ መኩሪያ ክንፈና አቶ አክሊሉ ጌታነህን በኢትዮ-ጅቡቲ መሥመር የደወሌና ጋላፊ ኬላዎች ላይ ነው ያገኘናቸው።
አሽከርካሪዎቹ ኮቪድ-19 ከተከሰተ ጀምሮ በጅቡቲም ሆነ በኢትዮጵያ በኩል በማኅበረሰቡ ዘንድ መገለል እየደረሰባቸው መሆኑን ይናገራሉ።
በዚህም ምግብ እንዳያገኙ ከማድረግ ጀምሮ በከተሞች ላይ እንዳይቆሙ በፖሊስ ክልከላ እየተደረገባቸው መሆኑን ነው በቅሬታ አቅርበዋል።
ቤተሰቦች እንዳሏቸውና ወረርሽኙ እንዳይዘመት ለራሳቸው ጥንቃቄ እያደረጉ ስለመሆኑ የሚገልጹት አሽከርካሪዎቹ፤ በጅቡቲ ውስጥ ያለው የመንገድ ብልሽትና አስቸጋሪውን በረሃ ተቋቁመው እየሰሩ በኅብረተሰቡ በዚህ ሁኔታ መታየታቸው አግባብ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
በተለይ ምግብ እንዳያገኙ ተፅዕኖ እየደረሰባቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የከባድ መኪኖች አሽከርካሪዎች ማኅበር ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዲስ ዓለማየሁ በድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው እንግልት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ የቀደመ ነው ባይ ናቸው።
"የአገሪቷን ወጭና ገቢ ንግድ የሚያንቀሳቅሱ አሽከርካሪዎች ይዘረፋሉ፣ ይደበደባሉ" የሚሉት አቶ አዲስ በኢትዮጵያም ሆነ በጅቡቲ መንግሥት በኩል ተገቢ ትብብር ይደረግላቸው እንዳልነበር ገልጸዋል።
ከ15 ቀናት በፊትም በምዕራብ ሐረርጌ ቁልቢ ከተማ ላይ ድብደባ የደረሰበት የከባድ መኪና አሽከርካሪ እጁን ተሰብሮ ማሽከርከር እንዳልቻለ በአካል መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።
አቶ አዲስ አሽከርካሪዎች በሄዱባቸው ከተሞች ሁሉ ተገቢውን ክብርና ትብብር ሊደረግላቸው እንደሚገባ ይገልጻሉ።
በአሽከርካሪዎች ላይ እንግልት እየደረሰ ነው የሚለውን ሀሳብ የሚጋሩት የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሉጬ፤ ማኅበረሰቡ ተገቢውን ክብርና የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዳይነፍጋቸው ጥሪ አቅርበዋል።
"ሁሉም ዜጋ ሀሩሩን ተቋቁመው የአገሪቷን ምጣኔ ሀብት ከሚያንቀሳቅሱ ባለሙያዎች ጎን ሊቆም ይገባልም" ብለዋል።
ፌዴሬሽኑም የግንዛቤ ማስጨበጫ ቅስቀሳ ማድረጉን፣ በደወሌና ጋላፊ ፍተሻ ጣቢያዎች በመገኘትም ከ700 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የኬሚካል፣ የውኃ መያዣዎች፣ ሳኒታይዘር፣ የሙቀት መለኪያዎችና ሌሎች ግብዓቶችን ማበርከቱን ገልጸዋል።