በኢትዮ- ጅቡቲ የድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች መቆሚያ መገንባቱ ለአሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ደህነንት ከፍተኛ ፋይዳ አለው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮ- ጅቡቲ የድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች መቆሚያ መገንባቱ ለአሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ደህነንት ከፍተኛ ፋይዳ አለው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2012 (ኢዜአ) በኢትዮ- ጅቡቲ የድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች መቆሚያ መገንባቱ ለአሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ደህነንት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የሶማሌ ክልል በበኩሉ የከባድ ተሽከርካሪዎች መቆሚያ መገንባቱ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን አስታውቋል።
ወደብ አልባዋ አገር ኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግዷን ለማሳለጥ የጅቡቲን ወደብ የምትጠቀም ሲሆን ለዚህ የሎጅስቲክስ አገልግሎት ደግሞ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ።
እነዚህ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ደርሶ ለመመለስ ቢያንስ አምስት ቀናት የሚፈጅባቸው ሲሆን በወረፋና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ግን ለሣምንታት በጎረቤት አገር ጅቡቲ መጉላላት ይገጥማቸዋል።
በኢትዮጵያ ጠረፍ አቅራቢያ ለመኪኖች ማቆሚያ የሚሆን ማዕከል አለመኖሩም የአሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪዎች ደህንነት ሥጋት ውስጥ መቆየቱ ይነገራል።
ከሰሞኑ ታዲያ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቁጥጥርም ሆነ ዘላቂነት ያለው የድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች መቆሚያ ለመገንባት በደወሌና ጋላፊ መስመሮች ላይ በሶማሌና አፋር ክልሎችና በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊዎች የቦታ ርክክብ ተፈጽሟል።
በዚህም በድሬዳዋ መውጫ ደወሌ ጠረፍ ላይ የዘጠኝ ሄክታር መሬት ከሶማሌ ክልል፤ በሠመራ መውጫ ደግሞ የጋላፊ ኬላ አቅራቢያ ለጊዜው ስፋቱ ይፋ ያልሆነ ሰፊ ቦታ በአፋር ክልላዊ መንግሥት በነፃ ተበረክቷል።
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ይርጋለም ሰፋኒ ለኢዜአ እንዳሉት የተመረጠው ሥፍራ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ደህንነትን የሚያስጠብቅ፣ የሎጀስቲክስን አገልግሎት የሚያፋጥን እንደሆነ ይናገራሉ።
የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበርን ያቀፈው ፌዴሬሽኑም ማዕከሉን ለመገንባት መወሰኑ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው አመላካች እንደሆነም ገልጸዋል።
አሽከርካሪዎች ማደሪያ በማጣት ሲሳቀቁ እንደነበረና ለዝርፊያም እንደሚጋለጡ አስታውሰው፣ ጠረፍ ላይ የመቆሚያ ማዕከል ከተገነባ ለወቅታዊ የኮሮናቫይረስ ቁጥጥር ብሎም ለዘላቂ ሎጀስቲክስ አገልግሎት ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን አመልክተዋል።
አንደኛው ማዕከል የሚገነባበት የደወሌ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ መሐመድ ሁሴንም የአሽከርካሪዎች ማረፊያ መገንባቱ ለአካባቢው የሚያመጣው ዕድል የሰፋ ስለመሆኑ አመልክተዋል።
የሶማሌ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮብለ መሐመድ በኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር ላይ ማዕከሉ መገንባቱ ሥፍራው ወደ ከተማነት እንዲያድግ፣ የአገርን ሀብት በአገር ውስጥ ለማፍሰስ እንደሚያግዝና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያመጣ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ኮቪድ-19ን ለመከላከል አሽከርካሪዎች ያለ ረዳት ወደ ጅቡቲ እንዲሄዱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
"ተሽከርካሪዎች ሲገቡና ሲወጡም የኬሚካል ርጭት ይደረጋል" ብለዋል።
የመቆሚያ ማዕከሉ አሽከርካሪዎች የጭነት ተራቸውን የሚጠብቁበት ከመሆኑ በተጨማሪ የመታጠቢያ፣ የማረፊያ፣ የምግብ፣ የጤና ምርመራና ሕክምና እንዲሁም ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
በቀጣይ በፍተሻ ጣቢያዎች አቅራቢያ የተሽከርካሪ መቆሚያ ተርሚናል ተገንብቶ አሽከርካሪዎች ሕክምና ተድርጎላቸው ውጤታቸውን የሚያውቁበት አሰራር እንደሚኖርም አቶ አብዲሳ አመልክተዋል።
በመሆኑም በወራት ውስጥ ቀሪው ጥናት ተጠናቆ በጀት ተመድቦለት የመሬት ጠረጋ ሥራዎች እንደሚጀመሩ አረጋግጠዋል።